ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በአሜሪካ የበላይነት የሚዘወር ዓለም አብቅቶለታል- ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ
ዴሜትሪ፤ “ምዕራባውያንበሩሲያ ላይ የሚጥሉት ማዕቀብ የራሳቸውን ኢኮኖሚ የሚያደቅ መሆኑን አልገባቸውም ብለዋል
አሜሪካና አጋሮቿ በዩጎዝላቭያ እንዳደረጉት አንደፈለጉ የሚፈነጩበት ዓለም አሁን የለም ብለዋል
ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በአሜሪካ የሚዘወር ዓለም እንደሌለ የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ ተናገሩ።
ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ ይህንን ያሉት በታሪክ በከፍተኛ ሁኔታ ሻክሯል ተብሎ እየተነገረለት ስላለው የሩሲያ-አሜሪካ ግንኙነትን በማስመልከት ከሩሲያው አርቲ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።
የፑቱን ቀኝ እጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞ ፕሬዝዳንት እንዲሁም የወቅቱ የሩሲያ ብሄራዊ ደህንነት ምክትል ኃላፊ ሜድቬዴቭ፤ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ እያንጸባረቁት ያለውን ጥላቻና ዛቻ ሩሲያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን አጠናክረው ምዕራበውያን እንዲጋፈጡ እንድል የፈጠር ነው ብለዋል።
ምዕራባውያን ከዩክሬን ጋር በተያያዘ በሞስኮ ላይ እየጣሉት ያለውን ማዕቀብ “አልገባቸውም እንጅ የራሳቸው ኢኮኖሚ የሚያደቅ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
አሜሪካ ቀደም ባሉ ዘመናትም ቢሆን የራሷን ፍላጎት ለማሟላት በመልክዓ ምድርም ጭምር ምንም ግንኙነት በሌላቸው እንደ በዩጎዝላቪያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን በመሳሰሉ ሀገራት ህገ ወጥ ድርጊቶች ስትፈጽም ብትቆይም፤ የምዕራቡ ዓለም ትንፍሽ ሳይል ቆይቶ አሁን ላይ ሩሲያ ለደህንነቷ በምታደርገው ዘመቻ መረባረቡ የሚያስተዛዝብ ነው ብለዋል ሜደቬዴቭ።
ይህ ለምን ይሆናል..? የሚል ጥያቄ በስሜት የሚያነሱት ሜድቬዴቭ፤ ምክንያቱም “አሜሪካ ዓለምን የምዘውረው እኔ ነኝ” ብላ ስለምታስበ ነው የሚል ምላሽም ይሰጣሉ።
ሜድቬዴቭ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በአሜሪካ የሚዘወር ዓለም የለም አብቅቶለታል ሲሉም አክለዋል።
ከምስራቁ ካምፕ እና ከሶቭየት ራሽያ መፈረካከስ በኋላ አሜሪካ ራሷን የዓለም ኃያል አድርጋ ታስባለች ያሉት ሜድቬዴቭ በዚህ ዘመን ህልሟን እውን ለማድረግ አትችልም ሲሉም ተናግረዋል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ “በዩጎዝላቭያ እንዳደረጉት አንደፈለጉ የሚፈነጩበት ዓለም አሁን የለም” የሚል ማስጠንቀቅያ አዘል አስተያየትም ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ ሰንዝረዋል።
እንደ ቻይና፣ ህንድ እና ሩሲያ የመሳሰሉ ኃያላን ሀገራት ባሉበት፤ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ስህበቱ አሜሪካኖች ከሚያስቡት በተለየ መልኩ የመሆን አድሉ ከፍተኛ መሆኑንም ጭምር አስረድተዋል።