የሩሲያው ፕሬዝዳንት ዶላር የሚታመን የመገበያያ ገንዘብ እንዳልሆነ ገልጸዋል
በሩሲያ አንድ ዩሮ 144 ነጥብ 66 ሩብል ይመነዘር የነበረ ቢሆንም አሁን ግን መቀነሱ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም አንድ ዶላር 99 ነጥብ 50 ሩብል ሲመነዘር ቢቆይም አሁን 93 ሩብል እየተመነዘረ እንደሆነ የሩሲያው አርቲ ዘግቧል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ በኋላ ሀገራቸው ነዳጅን በውጭ ሀገራት መገበያያ ገንዘብ ሳይሆን በራሷ ሩብል እንደምትሸጥ ገልጸው ነበር።
እንደ ሩሲያ ቱዴይ (አርቲ) ዘገባ ከሆነ ሞስኮ ከዚህ በኋላ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ጋር በዩሮም ሆነ በዶላር የመገበያየት ስሜት የላትም።
ቭላድሚር ፑቲን ዶላር የሚታመን የመገበያያ ገንዘብ እንዳልሆነ ከተናገሩ ከቀናት በኋላ ዶላርና ዩሮ ከሩብል ጋር ያላቸው ምንዛሬ ቀንሷል ተብሏል።
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ እና የካቢኔ አባላት ከአውሮፓ ጋር በሩብል የሚካሄደውን ግብይት በተመለከተ በአንድ ሳምንት ውስጥ ውሳኔ እንዲያስቀምጡ ፑቲን ትዕዕዝ ሰጥተው ነበር።
ዩሮና ዶላር ከሩብል ጋር ያላቸው የምንዛሬ መጠን መቀነሱን ሩሲያ ቱዴይ የዘገበ ሲሆን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ግን በዚህ ጉዳይ ያሉት ነገር የለም።
በዩክሬንና በሩሲያ መካከል የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ ሩሲያ ከምዕራቡ ዓለም የሚሰነዘርባትን ማዕቀብና እገዳ ለመቋቋም ጥረት እያደረገች ነው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምንም እንኳን የተለያዩ ሀገራት የሀገራቸውን ሀብት ቢያግዱም ሞስኮ ግን በገባችው ውል መሰረት የነዳጅ አቅርቦትን ትቀጥላለች ማለታቸው ተገልጿል።