የትግራይ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የያዙት አቋም የፖለቲካ ቀውሱን የሚያባበስ ነው ሲሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለጹ
ፓርቲዎቹ በሁለቱ የህወሓት ቡድኖች መካከል የሚየታየው ውዝግብ ከስልጣን እንጂ ፍጹም ከህዝብ ፍላጎት የመነጨ አይደለም ብለዋል
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ወታደሩ ከአንድ ወገን የፖለቲካ ውግንና ይልቅ የጋራ መፍትሄ እንዲፈጠር ግፊት ማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቀዋል
የፕሪቶሪውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ከአመታት ጦርነት በኋላ በጊዜያዊ አስተዳደር እየተመራ በሚገኝው የትግራይ ክልል የሚስተዋለው የፖለቲካ ትኩሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል፡፡
በአቶ ጌታቸው ረዳ እና በደብረጽዮን ገ/ሚካኤል(ዶ/ር) በሚመሩት የህወሓት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው የአስተዳደር እና የስልጣን ውዝግብ ከጦርነት በቅጡ ባላገገመው ክልል ላይ ተጨማሪ ቀውስን እንዳያወልድ ከፍተኛ ስጋትን ጭሯል፡፡
የትግራይ ሠራዊት አዛዦች ሐሙስ ጥር 15/2017 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ በዶ/ር ደብረጺዮን ለሚመራው የህወሓት ቡድን ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው"ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የተሰጠው ተልዕኮ ውጪ ክህደት በመፈጸም ለውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን እየሰራ ይገኛል" ሲሉ ከሰዋል።
አመራሮቹ 14ኛ ጉባኤውን ያደረገው ህወሓት ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማስተካከል የወሰነው ውሳኔ "ሳይውል ሳያድር ተግባራዊ እንዲደረግ" የትግራይ ሰራዊት ድጋፍ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወታደራዊ አመራሮቹ ውግንና የክልሉን የፖለቲካ ቀውስ ሊያባብሰው እንደሚችል ስጋታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
የባይቶና ትግራይ ምክትል ሊቀመንበር ዮሴፍ በርኸ አሁን እየታዩ ያሉ ክፍፍሎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲመሰረት ከ98 በመቶ በላይ ስልጣኑን ለህውሓት በመሰጠቱ የተፈጠረ ነው ይላሉ፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተጠያቂነትን ለማስፈንና እና የድህረ ጦርነት ችግሮችን ለመቅረፍ በሚያስችል መልኩ ተዋቅሯል ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት
አቶ ዮሴፍ፤ በአሁኑ ወቅት ስልጣን ከጃችን ወጥቷል የሚሉ አካላት በዋናነት ስልጣንን ብቻ ታሳቢ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ በር ከፍቷል ባይ ናቸው፡፡
“በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በእነደብረጽዮን ቡድን መካከል ያለው ክፍፍል አንድ እና አንድ ስልጣንን ከመሻት የመነጨ ነው፤ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ያልተፈጸሙ በአስተዳደሩ ድክመት ያልተከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን እኛም የምንጋራው ሀሳብ ነው። መዋቅሩም ጠንካራ ነው ብየ ለመናገር አልደፍርም፤ግን ደግሞ በተገቢው መንገድ እድል ተሰጥቶታል ብለን አናምንም” ብለዋል፡፡
አስተዳደደሩ አመራሮችን ለመሾም እና መዋቅሩን ለማደረጃት በሚያደርገው ጥረት መደበኛ ጉባኤ አካሂጃለሁ የሚለው የህውሓት ጽህፈት ቤት ከአንዳንድ ወታደራዊ አመራሮች ጋር በመሆን እንቅፋት ሲሆን መቆየቱን አቶ ዮሴፍ ያነሳሉ። ይህም የሚጠበቅበትን ያክል እንዳይንቀሳቀስ ፈተና መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
“ለወረዳም ሆነ ለዞን አመራሮችን ሲመድብ በማስፈራራት እና ለ30 አመታት በዘረጉት ረጅም ኔትዎርክ በተለያዩ መንገዶች ሀላፊዎች ቢሮ እንዳይገቡ ያደርጋሉ፤ ይህ በግልጽ ስለታየ ነገርኩህ እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እግሩን እንዳይተክል ተንሳፎ እንዲቀር ያደረጉት ከእነደብረጽዮን ቡድን ጋር የሚሰሩ ወታደራዊ አመራሮች ናቸው፤ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች አስተዳደሩ ስራውን በተገቢው መንገድ አልሰራም ብለው ሊጠይቁት አይችሉም መጠየቅ ካለበት የሚጠይቀው አሁን ከጦርነት በኋላ በድንኳን ውስጥ የሚኖር የትግራይ ህዝብ ነው” ሲሉ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ ፡፡
አቶ ዮሴፍ በርኸ አክለውም “ከሰሞኑ በግልጽ ወጥተው ስልጣኑን ለእነደብረጺዮን ቡድን እንድታስረክቡ ያሉት አካላት አሁን ላይ በይፋ ወጡ እንጂ ስልጣኑን ወደ ደገፉት ወገን ለመውሰድ በውስጥ ከጽህፈት ቤቱ ጋር በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል፤ እኛ እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ድርጊት ተቃውመነዋል። አስተዳደደሩ በተሰጠው ሀላፊነት መጠየቅ ካለበት ገለልተኛ በሆነ ምክር ቤት እንጂ በመከላከያ ሀይሉ አይደለም፤ ሰራዊቱ በፖለቲካ ውስጥ እጁን ሊያስገባ አይገባም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሳልሳይ ወያነ ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ ብርሀነ አጽበሀ የጥር 15ቱ የወታደራዊ አመራሮች መግለጫ ወታደራዊ አገዛዝን ወደ ትግራይ የመመለስ አዝማሚያ የታየበት ሲሉ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
“የአመራሮቹ እንቅስቃሴ ፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በግልጽ የሚጥስ ነው፤ ምንም እንኳን ስምምነቱ ሙሉ ለሙ ተግባራዊ ባይደረግም ቢያንስ አንጻራዊ ሰላም አምጥቷል፤ የትግራይ ህዝብ ደግሞ አሁን ተጨማሪ ጦርነት የሚያስተናግድበት አቅም የለውም፤ በእውነቱ የሰራዊቱ አመራሮች ለህዝብ የቆሙ ከሆኑ ይህን አጀንዳ ይዘው መምጣት የለባቸውም ነበር” ነው ያሉት፡፡
ወታደራዊ አዛዦቹ ባወጡት መግለጫ በቀጣዮቹ ቀናቶች ጊዜያዊ አስተዳደሩ የህውሓት ጠቅላላ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዲያደርግ አዘው የነበረ ቢሆንም፤ በጠበቁት ልክ በህዝቡ ዘንድ ድጋፍ ባለማግኝታቸው በአሁኑ ወቅት ድጋሚ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ አቶ ብርሀነ ይናገራሉ፡፡
“እንደተባለው አስተዳደሩን በኃይል ለማንሳት ይሞክራሉ ብየ አላስብም፣ ሰራዊቱም የስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ መሆን የለበትም፤ እንደዛ የሚሆን ከሆነ ግን ዳግም ጦርነትን የሚያስከትል ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱም በአስተዳደሩ ላይ ድምጽ ስላለው እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ዝም ይላል ብየ አልጠበቅም፤ ይህ ከመሆኑ እና ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ለመግባቱ በፊት ግን ወታደራዊ አመራሮች እጃቸውን ሰብስበው ፖለቲከኞቹ ልዩነታቸውን እንዲፈቱ መፍቀድ አለባቸው” ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ የትግራይ መከላከያ አመራሮች ያወጡት መግለጫ የሁሉም አመራሮች አቋም እንዳልሆነ የሚገልጹት ደግሞ የባይቶና ትግራይ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ ናቸው፡፡
ከአመራሮቹ መካከል ፖለቲከኞቹ ችግራቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ እድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ ከዚህ በተቃራኒው ያለው ውሳኔም የህዝቡንም የክልሉንም ጥቅም የማያስጠብቅ እና ተጨማሪ ቀውስን የሚያዋልድ እንደሚሆን ተቃውሟቸውን የገለጹ አመራሮች እንዳሉ መረጃው እንዳላቸው ምክትል ሊቀመንበሩ አንስተዋል ፡፡
“መግለጫ የሰጡት አመራሮች በእነርሱ ዘንድ ዋናው ህውሓት ተብሎ የሚጠራው ለ30 አመታት በፖለቲካ ስልጣን ውስጥ የነበረው አካል ስልጣኑን እያጣ ከመጣ እኛም ስልጣን አይኖረንም የሚል ስጋት አለባቸው፤ ይህን ሀሳባቸውን ለማስፈጸም በሰራዊቱ ውስጥ አካባቢ እና አውራጃን መሰረት ያደረገ ግንኙነትን ለመፍጠር ጥረት ላይ ናቸው ይህ ደግሞ ክፍፍሉን በማስፋት ችግሩን ይበልጥ የሚያባብስ አደገኛ አካሄድ ነው” ባይ ናቸው፡፡
ከመነሻው የፓርቲው ክፍፍልም ሆነ የወታደራዊ አመራሮቹ ውዝግብ ከህዝብ ጥቅም ሳይሆን ስልጣን ከመቆጣጠር መነሻውን ያደረገ መሆኑ አደገኛ እንደሚያደርገው አቶ ዮሴፍ ያነሳሉ፡፡
“ክልሉ በርካታ የጸጥታ ችግሮች አሉበት ፣ የምግብ እጥረት ያለባቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ተፈናቃዮችም ሙሉለሙሉ ወደ መኖሪያቸው አልተመለሱም ፣ በተለያዩ አካላት ተይዘው የሚገኙ የክልሉ ይዞታዎችም በጦርነቱ ወቅት በነበሩበት ናቸው ያሉት፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ነው እንግዲህ ለህዝብ የተቆረቆሩ መስለው በዋነኛነት ስልጣንን በማካለ ጥያቄ ላይ እየተወዛገቡ ያሉት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አክለውም ሁኔታው በጊዜ የማይቆም ከሆነ ከጦርነት ያላገገመውን ህዝብ እና ያልተረጋጋውን ፖለቲካ ወደ ተጨማሪ ቀውስ የሚያስገባ እንደሆነ ገልጸው ለአንድ ቡድን ተብሎ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ማፍረስ “እንደ ህዝብ ሊጎዳን ይችላል” ብለዋል፡፡
ባይቶና ትግራም ሆነ ሌሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጊዜያዊ አስተዳደሩ በካቢኔው ውስጥም ሆነ በአስተዳደር መዋቅሩ አካታች ሊሆን እንደሚገባው እንዲሁም አፈጻጸሙን የሚቆጣጠረው ገለልተኛ ምክር ቤት መቋቋም እንደሚኖርበት የጋራ አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል::
የሳልሳይ ወያነ ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊአቶ ብርሀነ በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ፤ ከዚህ ባለፈ ግን በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ውስጥ የተካተቱ ባለድርሻ አካላት የፌደራል መንግስት ፣ የአፍሪካ ህብረት ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ጉዳዩን በቅርበት መከታተል እንዳለባቸው እንዲሁም ሁለቱ ወገኖች ወደ ስምምነት በሚቀራረቡበት መፍትሄ ዙሪያ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡