የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የማስገባት ስራ በትግራይ ክልል ተጀመረ
ተዋጊዎች ወደ ተሀድሶ ማዕከላት ከመግባታቸው በፊት በእጃቸው ላይ የሚገኝውን የነፍስ ወከፍ እና የቡድን ጦር መሳርያዎች አስረክበዋል
በመጀመርያ ዙር የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተንና ወደ ማህበረሰቡ የማቀላቀል ስራ 75 ሺህ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ተገልጿል
የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የማስገባት ስራ በትግራይ ክልል መጀመሩን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቀ።
በዚህም የመጀመሪያውን ዙር ለተሀድሶ ስልጠና የሚገቡ የቀድሞ ተዋጊዎች የነፍስ ወከፍ እና የቡድን ጦር መሳሪያዎች ርክክብም አካሄደዋል።
ርክክቡ የተሀድሶ ኮሚሽን አመራሮችን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት፣ የመንግስታቱ ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች በተገኙበት ተከናውኗል።
በመቐሌ፣ እዳጋ ሀሙስ እና ዓድዋ የመጀመሪያ ዙር ተዋጊዎች ስልጠና የሚወስዱባቸው ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ኮሚሽኑ በትናንትናው ዕለት ማስታወቁ ይታወሳል።
በተዘጋጁ ሶስት ማዕከላት በሚቀጥሉት አራት ወራት 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በዘላቂነት የማቋቋምና ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ እንደሚከናወን ይጠበቃል።
የቀድሞ ተዋጊዎች በተዘጋጁ ማዕከላት ስልጠናዎችን ከወሰዱ በኋላ የመቋቋሚያ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ እንደሚደረግ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከሰባት ክልሎች ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማዕከላት ለማስገባት የመለየት ሥራ ማጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 274 ሺህ ታጣቂዎች የሚገኙት በትግራይ ክልል መሆኑ ታውቋል።
ስራውን ለማከናወን ከመንግስት እና ከተለያዩ አጋር አካላት የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገለት ያስታወቀው ኮሚሽኑ በቀጣይ 12 ሀገራት ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን መግለጹ አይዘነጋም።
የሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ለሁለት አመታት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በህዳር 2015 በፕሪቶሪያ በተካሄደው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ተቋጭቷል።
በዚህ ሰምምነት መሰረት ህወሓት ትጥቅ ለመፍታታ የተስማማ ሲሆን የፌደራል መንግስት ይህን እንዲያስፈጽም ኮሚሽኑን ማቋቋሙ ይታወሳል።