ፕሬዘዳንት ፋርማጆ የሶማሊያ ባህር ሀይል ዋና አዛዥንም ከስልጣን አንስተዋል
የሶማሊያ ፕሬዘዳንት መሃመድ ፋርማጆ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አገዱ፡፡
ፕሬዘዳንት መሃመድ አብዱላሂ ወይም መሃመድ ፋርማጆ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሁሴን ሮብልን ከስልጣን ማገዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣናቸው የታገዱት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡ፕሬዘዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶማሊያ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡
የሶማሊያ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ መካሄድ ያለበት ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተራዝሟል፡፡
በምርጫው መራዘም ምክንያትም የፕሬዘዳንት መሃመድ ፋርማጆ ስልጣን ተራዝሟል በሚል ወደ ግጭት የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ ሁሴን ሮብል በመጨረሻም በተደረገ ውይይት ሁለቱ መሪዎች ሰላም አውርደው ነበር፡፡
ፕሬዘዳንት መሀመድ ፋርማጆ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የሙስና ወንጀል ምርመራ ላይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ስልጣናቸው ታግዷል፡፡
የሶማሊያ ሁለቱ መሪዎች ዳግም ወደ ግጭት መግባት ፕሬዘዳንታዊ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በሀገሪቱ ግጭት እንዳይቀሰቀስ ተሰግቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስት መሃመድ ሁሴን ሮብል ባሳለፍነው እሁድ ፕሬዘዳንቱ የሶማሊያምርጫን ለማጭበርበር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወኑ ነው በሚል ተችተዋል፡፡
የሁለቱ መሪዎች አለመግባባት በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር (አሚሶም) እና ሌሎች አጋር ሀገራት እርዳታ ከዋና ዋና ከተሞች የተመታው አልሻባብ መልሶ እንዳይደራጅ ስጋትን ፈጥሯል፡፡
ፕሬዘዳንት ፋርማጆ የሶማሊያ ባህር ሀይል ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱልሀኪም መሀመድ ድሪር ከሙስና ወንጀል ጋር ተጠርጥረዋል በሚልም ከስልጣን አንስተዋል፡፡