ፑቲን ዩክሬንን ለማጥቃት 'አዲስ ሚሳኤል' መጠቀማቸውን አረጋግጠው ምዕራባውያንን አስጠንቅቀዋል
ፑቲን ሩሲያ በሰከንድ 3 ኪ.ሜ የሚከንፍ አዲስ የመካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል መጠቀሟን አረጋግጠዋል
ፑቲን “ሚሳዔሎቻችንን ማንም ሊያስቆማቸው አይችልም፤ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ዝተዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላደሚር ፑቲን፤ ሀገራቸው የዩክሬኗ ዲኒፕሮን ያጠቃችው 'አዲስ ሚሳኤል' በመጠመም መሆንን በማረጋገጥ ምዕራባውያንን አስጠንቅቀዋል።
ፑቲን ማምሻውን ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ ዩክሬን ሩሲያን ለማጥቃት የአሜሪካ እና የብሪታኒያ የረጅም ርቀት ሚሳዔሎችን መጠቀሟን አረጋግጠዋል።
የረዥም ርቀት የጦር መሳሪያዎች በጦር ሜዳ ያለውን ጨዋታ አይቀይረውም ያሉት ፑቲን፤ ሩሲያ ወታደሮች አሁንም ወደፊት እየገፉ ነው ብለዋል።
ፑቲን ለምእራባውያን ሀገራትም የማስጠንቀቂያ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ማንኛውም ጠብ አጫሪ እንቅስቀሴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን ሲሉም ዝተዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለውም፤ “አሜሪካ በፈረንጆቹ 2019 የተፈረመውን የሚሳዔል ስምምነት በመጣስ ትልቅ ስህተት ሰርታለች” ሲሉም ተናግረዋል።
“በሩሲያ ላይ ለሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት ሁሌም መልስ አለ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “ለማንኛውም ሁኔታ ዝግጁ ነን፤ የሩሲያን መልስ የመስጠት አቅም ማንም ሰው ሊጠራጠር አይገባም” ብለዋል።
ሩሲያ በዛሬው እለት አዲስ የመካከለኛ ርቀት ሚሳዔል በመጠቀም በዩክሬን ላይ የወሰደችው እርምጃም፤ ዩክሬን የአሜሪካ እና የብሪታኒያ ሚሳዔሎችን በመጠቀም ለፈጸመችው ጥቃት መልስ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሩሲያ በዛሬው እለት አዲስ የመካከለኛ ርቀት የባላስቲክ ሚሳዔል መጠቀሟን ያረጋገጡት ፑቲን፤ ሚሳዔሉ በአንድ ሰከንድ ከ2.5 እስከ 3 ኪሎ ሜትር የሚከንፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሩሲያ ከዚህ በኋላ ለሚፈጸምባት ማንኛውም ጥቃት ከባድ መሳሪያ ለመጠቀም እንደምትገደድ ያስታወቁት ፑቲን፤ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እንደምትሰጥም አስታውቀዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንቱ ቭላድሚር ፑቲን ባሳለፍነው ማክሰኞ የተሻሻለውንና የሩሲያን የኒዩክሌር መሳሪያ አጠቃቀም የሚወስነው ህግ ማጽደቃቸው ይታወሳል።
ሩሲያ በ2020 በይፋ ያወጣችውን የኒዩክሌር ህግ ማሻሻሏን ስትገልጽ የቆየች ሲሆን፥ ባይደን ለኬቭ ይሁንታ በሰጡ ማግስት ነው ፑቲን ማሻሻያውን ያፀደቁት።
ማሻሻያው ኒዩክሌር ያልታጠቁ ሀገራት ከታጠቁት ጋር በመተባበር በሩሲያ ላይ ጥቃት ካደረሱ በሞስኮ ላይ “የጋራ ጥቃት” እንደከፈቱ ይቆጠራል የሚል ሃሳብ አካቷል።
ሩሲያ የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን መቼ መጠቀም እንዳለባት በግልጽ የሰፈረበት ህግ፥ ድንበር አቋራጭ የሚሳኤል፣ የአየር እና ድሮን ጥቃት ከተፈጸመባት አውዳሚዎቹን መሳሪያዎች መጠቀም እንደምትጀምር የሚፈቅድ ነው።