ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ስልጣን ከያዙ በኋላ ያደረጉት የመጀመሪያው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ነው
አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ስልጣን ከያዙ በኋላ ያደረጉት የመጀመሪያው ይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ ቆይታውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ እና በሳፋሪ ኮም ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ ላይ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አክለውም “ከኢትዮጵያ ጋር ባለን ግንኙነት የጋራ ጥቅሞችን ለማስከበር አዳዲስ ግንባሮችን እየፈለግን ነው” ብለዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሁለቱ ሀገራት የጋራ ብልጽግና ለመስራት እንደሚሰሩ አረጋጠዋል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በቅርቡ ከፍራንስ-24 ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው ማንኛውም ነገር ወደ ኬንያ ይደርሳል” ማለታው ይታወሳል።
ዊሊያም ሩቶ፤ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት መፍትሄ ማግኘት በሚቻልበት ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲርል ራማፎሳ፣ ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ እና ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንክን መወያየታቸውም አስታውቋል።