የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “ህይወት ሞትን እንደሚያሸንፍ ሁሉ ዩክሬን በእርግጠኝነት ታሸንፋለች” አሉ
ፕሬዝዳንቱ የፋሲካን በዓል ምክንያት በማደረግ ባለታላፉት መልእክት “ጌታና ቅዱሱ ሰማያዊ ብርሃን ከእኛ ጋር ናቸው” ብለዋል
ፈተና ቢበዛም ዩክሬናውያን በያዙት ትክክለኛ መንገድ መጨረሻ ላይ እንዲደርሱ ፐሬዝዳንት ዘለንስኪ ጠይቀዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ የፋሲካን በዓል ምክንያት በማደረግ ባስለታለፉት መልእክት “ህይወት ሞትን እንደሚያሸንፍ ሁሉ ዩክሬን በእርግጠኝነት ታሸንፋለች” ብለዋል።
ዘለንስኪ በጥንታዊቷ ቅድስት ሶፊያ ካቴድራል ተገኝተው ንግግር “ታላቁ በዓል ዛሬ ታላቅ ተስፋን እና የማይናወጥ እምነትን ይሰጠናል፤ ብርሃን ጨለማን እንደሚያሸንፍ፣ መልካምነት ክፋትን እንደሚያሸንፍ፣ ህይወት ሞትን እንደሚያሸንፍ ሁሉ ዩክሬን በእርግጠኝነት ታሸንፋለች” ሲሉ ተደምጧል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “ጌታና ቅዱሱ ሰማያዊ ብርሃን ከእኛ ጋር ናቸው” ብሏል።
“በጣም አስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ እየገባን ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “በዚህ በያዝነው ትክክለኛ መንገድ መጨረሻ ላይ እንደርስ” ሲሉም ለዩክሬናውያን ጥሪ አቅረበዋል።
ዘለንስኪ "በፋሲካ ህልማችን እውን እንዲሆን ታላቅ ጸጋን እግዚአብሔርን እንጠይቃለን" ሲሉም አክለዋል።
በተያያዘ፤ ፕሬዝዳንቱ በዛሬው እለት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲንን በኪቭ ተቀብለው እንሚወያዩ አስታውቋል።
ከባለስልጣናቱ ጋር በሚኖራቸው ውይይት ዩክሬን በፍጥነት እንዲሟሉ የምትፈልጋቸውን “ከባድ የጦር መሳሪያዎችን” ጉዳይ አብይ አጀንዳ ይሆናል ብለዋል።
አሜሪካ እና የኔቶ አጋሮች ከባድ መሳሪያዎችንና የላቀ የጦር መሳሪያ ስርዓቶችን ለዩክሬን ለማቅረብ ያላቸውን ዝግጁነት አሳይቷል።ብሪታንያም እንዲሁ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ለመላክ ቃል ገብታለች።
ሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት አሁንም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።
እንደ አሜሪካ ባለስልጣናት ሁሉ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ሞስኮ እና ኪቭ በማቅናት በሀገራቱ መካከል ያለውንና የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን ጦርነት ለማርገብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሀገራቱ ፕሬዝዳንቶች ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጉቴሬዝ በመጪው ማክሰኞ ወደ ሞስኮ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚወያዩ የዋና ጸሃፊው ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።