ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ጦር በፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የሚመራውን የመንግስት ስልጣን እንዲቆጣጠር ጥሪ አቀረቡ።
እስካሁን በነበረው ጦርነት በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠሯን ያስታወቀችው ሩሲያ የዘለንስኪ ስልጣን በወታደሩ እጅ እንዲገባ ጥሪ አቅርባለች።
- ሊያስቆመን የሚሞክር ማንኛውም አካል በታሪኩ አይቶት የማያውቀው እጣፋንታ ይገጥመዋል-ፑቲን
ክሬምሊን ይህንን ያለችው የሩሲያ ጦር ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኬብ እየተቃረበ ባለበት ወቅት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል። አሁን ላይ የሩሲያ ጦር በሰሜናዊ ኬቭ አቅራቢያ ላይ መድረሱንና የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እየወጡ ስለመሆኑ ተዘግቧል።
በኬቭ አቅራቢያ የሚገኘው ሆስትሜል የሚባለው የአየር ኃይል ማዘዣ ጣቢያ በሩሲያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው በኬቭ አቅራቢያ የሚገኘው ሆስትሜል የሚባለው የአየር ኃይል ማዘዣ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ሲውል በሩሲያ በኩል ምንም ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል።
የዩክሬን ጦር ተሽከርካሪዎች የኬቭ ከተማን ለመከላከል እየገቡ መሆኑም ተዘግቧል። ዩክሬን 18 ሺህ ጠብመንጃ ለበጎ ፈቃደኞች መስጠቷንም የሀገር ውስጥ መስሪያ ቤቷ አስታውቋል።
የብሪታኒያ ጦር እንዳስታወቀው በዚህ ጦርነት እስካሁን 450 የሩሲያ ወታደሮች፣ 194 ዩክሬናውያን እና 57 ንጹሃን መገደላቸውን ሲገልጽ ዩክሬን ደግሞ 1000 ሩሲያውያን መሞታቸውን ገልጻለች።
ከሰዓት በኋላ በወጡ መረጃዎች መሰረት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በቤላሩስ መዲና ሚኒስክ ለመነጋገር ዝግጁ ናት። ንግግር እንዲደረግ በቅድሚያ ፍላጎት ያሳዩትና ጥያቄ ያቀረቡት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ መሆናቸውንም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ጦርነቱን ተከትሎ ፖላንድ ከሩሲያ ጋር ያላትን የአየር ክልል ለመዝጋት ዝግጅት አድርጋለች ተብሏል። በጦርነቱ እስካሁን 100 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የኔቶ አባል ለመሆን ለሁሉም የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት ያቀረቡት ጥያቄ ሁሉንም አባል ሀገራት እንዳስፈራቸው መግለጻቸው ይታወሳል።