ፕሬዝደንት ትራምፕና ዘለንስኪ የማዕድናት ስምምነት በኃይትሀውስ ሊፈራረሙ ነው
ስምምነቱ ዩክሬን ጦርነቱን ለማስቆም ከሩሲያ ጋር ንግግር እያደረጉ ያሉትን ፕሬዝደንት ትራምፕን ድጋፍ መልሶ ለማግኘት ያስችላታል ተብሏል

ትራምፕ ቀደም ሲል ዩክሬን አሜሪካ ያደገችላትን በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች ድጋፍ በውድ ማዕድናት እንድትከፍል እንደሚፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል
ፕሬዝደንት ትራምፕና ዘለንስኪ የማዕድናት ስምምነት በኃይትሀውስ ሊፈራረሙ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪና ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በብርቅዬ የዩክሬን ማዕድናት ኢንዱሰትሪ ላይ መሳትፍ የሚያስችላትን ስምምነት በኃይት ሀውስ ሊፈራረሙ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
ስምምነቱ ዩክሬን ጦርነቱን ለማስቆም ከሩሲያ ጋር ንግግር እያደረጉ ያሉትን ፕሬዝደንት ትራምፕን ድጋፍ መልሶ ለማግኘት ያስችላታል ተብሏል።
ከባይደን አስተዳደር በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የመሳሪያና የሞራል ድጋፍ ሲያገኙ የቆዩት ዘለንስኪ የሶስት አመቱን ጦርነቱ በፍጥነት መጨረስ፣ ከሩሲያ ግንኙነታቸውን ማደስና ለዩክሬን በድጋፍ የፈሰሰውን ገንዘብ ለማስመለስ ከሚፈልጉት ትራምፕ ፍጹም ልዩ የሆነ አቋም አጋጥሟቸዋል። ትራምፕ ለአውሮፓ ደህንነት ያላቸው ቁርጠኝነት መቀነስና የአቋም ልዩነት አውሮፓውያን እንዲደናገጡና ዩክሬን ውስጥ ለሩሲያ የሚያደላ የሰላም ስምምነት ሊፈጸም ይችላል የሚል ፍርሃት እንዲነግስ አድርጓል።
በቅርቡ የተደረሰውና ዛሬ እንደሚፈረም የሚጠበቀው የብርቅዬ ማዕድናት ስምምነት አሜሪካ የዩክሬንን ማዕድናት እንድታገኝ የሚያስችል ሲሆን አሜሪካ በምትኩ ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና ለመስጠት ስለመስማማቷ በግልጽ የተባለ ነገር የለም። ትራምፕ አሜሪካ ከዩክሬን ጋር ያላት ግንኙነት መቀጠሏ እንደ ደህንነት ዋስትና ያገለግላል ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ ቀደም ሲል አሜሪካ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ያደገችላትን በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች ድጋፍ በውድ ማዕድናት እንድትከፍል እንደሚፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል።
ዘለንስኪ ሀገሪቱን ለቀጣይ ትውልዶች ለእዳ የሚዳርግ ስምምነት እንደማይፈርሙ ሲገለጹ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ቆየት ብለው ማዕድናቱን ከአሜሪካ ጋር በጋራ ለማውጣትና ለመጠቀም ተስማምተዋል። የዋሽንግተኑ ስብሰባ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ከትራምፕ ጋር መነጋገር ያለውን ጠቀሜታ ሲናገሩ ለነበሩት ዘለንስኪ ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ አለው ተብሏል።
የሩሲያና አሜሪካ ባለስልጣናት በቅርቡ በሳኡዲ አረቢያ ተገናኝተው በሁለትዮሽና ጦርነቱን በማስቆም ጉዳይ መክረዋል፤ በቅርቡም በድጋሚ ይገናኛሉ።
የሁለቱ ሀገራት ባለስጣናት ከተስማሙ በኋላ ፕሬዝደንት ትራምፕና ፑቲንም ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።