ዘለንስኪ ጦርነቱን ሊያስቆም ይችላል ያሉትን የሰላም እቅድ ለአሜሪካ ሊያቀርቡ ነው
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት ያስቆማል የተባለው እቅድ ለአሜሪካው ፕሬዝደንት እና ለ2024ቱ ምርጫ እጩዎች ይቀርባል ተብሏል
ዋሽንግተን በዚህ ጦርነት ዋነኛ የኬቭ አጋር በመሆን ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን እያደረገች ዘልቃለች
ዘለንስኪ ጦርነቱን ሊያስቆም ይችላል ያሉትን የሰላም እቅድ ለአሜሪካ ሊያቀርቡ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልደሚር ዘለንስኪ ከሩሲያ ጋር እየተደረገ የሚገኝውን ጦርነት ሊያስቆም ይችላል ያሉትን እቅድ ለአሜሪካ እንደሚያቀርቡ አስታወቁ፡፡
እቅዱ ለአሁናዊው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና ለ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ካማላ ሃሪስ እንዲሁም ዶናልድ ትራምፕ የሚቀርብ ይሆናል ነው የተባለው፡፡
ዘለንስኪ ጦርነቱን ያስቆማል ስላሉት እቅድ ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ ባያደርጉም በሩሲያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በማበርታት ወደ ድርድር እንድትመጣ ለማስቻል ያለመ ሊሆን እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በመጨረሻም ከሩሲያ ጋር የምንገኝበት ጦርነት በንግግር ሊጠናቀቅ የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንደደረሰ ይሰማኛል ያሉት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በእቅዱ ዙሪያ ከአሜሪካ አጋሮቻችን ጋር በጥልቀት የምንወያይበት ይሆናል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዚህ እቅድ ዋነኛ አላማ ሩሲያ ጦርነቱን እንድታቆም ጫና ማሳደር ነው ያሉ ሲሆን፤ በመጪው መስከረም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሚኖረው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ እቅዱን ለአሜሪካ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
በሰላም አቅዱ ዙርያ ከዋሽንግተን ሰዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የሞስኮ ልዑካን በተገኙበት ጦርነቱን ማቆም በሚቻልበት ሁኔታ መምከር እንደሚፈልጉም ነው የገለጹት፡፡
ዩክሬን የአለም መሪዎችን በማሰባሰብ በሲዊዘርላንድ ካዘጋጀቻቸው ሩሲያን ካላሳተፉ የሰላም ጉባኤዎች ወዲህ ከሞስኮ ልዑካን ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ፈቀደኝነቷን ስታሳይ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ዩክሬን የሩሲያን ድንበር ጥሳ በመግባት በኩርስክ ክልል ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ውይይት የሚታሰብ አይደለም ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በዩክሬን እና ፖላንድ ጉብኝት አድርገው የነበሩት የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ ከጉብኝታቸው መልስ ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ ጦርነቱን በሰላማዊ ንግግር ለመቋጨት ደልሂ ድጋፍ እንደምታደርግ ነግረዋቸዋል፡፡
ሞስኮ እና ኬቭ የድርደር እና ውይይት ሀሳቦችን ባነሱ ጊዜ ቀድመው የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ለመቀራረብ አመቺ እንዳልሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ የትኛውንም የሰላም ድርድር እና ተኩስ አቁም ከማድረጋችን በፊት በዩክሬን የተቆጣጠረቻቸው አራት ክልሎች የግዛቷ አካል ስለመሆናቸው እውቅና እንዲሰጣት ስትጠይቅ፤ ዩክሬን በበኩሏ የሞስኮ ጦር ቀድሞ ከነበረው የዩክሬን የግዛት ክልል ሙሉ ለሙሉ ካልወጣ መነጋጋር እንደማትፈልግ ትገልጻለች፡፡
በአሁኑ ወቅት 3 ሳምንታትን ባስቆጠረው የኩርስክ ክልል ጥቃት ኬቭ 1200 ስኩዌየር ኪሎሜትር የሩሲያ አካባቢዎችን መቆጣጠሯን ስታሳውቅ የሞስኮ ወታደሮች ከግዛታችን ሲወጡ እኛም አካባቢውን ለቀን እንወጣለን ብላለች፡፡