ሱዳናውያን ”ክብራችን ይመለስ” በሚል በመንግስታቸው ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ነው
ሱዳናውያን ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡ ካደረጋቸውስ ውስጥ አንዱ ገደብ ያጣውን የኑሮ ውድነት ነው
በሀገሪቱ የአንድ ዳቦ ዋጋ 50 የሱዳን ፓውንድ መግባቱ ተሰምቷል
ሱዳናውያን የሀገሪቱን በትረ-ስልጣን በጨበጠው ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሀንመንግስት ላይ የሚያሰሙት ተቃውሞ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።
ተቃዋሚዎቹ አልሲተን፣ ኦማክና አል-ማሽታል፣ የመሳሰሉ ዋና ዋና የካርቱም መንገዶች መዝጋታቸውንም ነው የተገለጸው።
“ወታደራዊ አገዛዝ ያብቃ፣ የዳቦ የዋጋ ጭማሪ ተቀባይነት የለውም እና ክብራችን ይመለስ” ቀደም ካሉ ወራት አንስቶ እስከ ዛሬዋ እለት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በሀገሪቱ ከተሞች ላይ ባደረጓቸው ተቃውሞዎች ሲያንጸባርቋቸው የተሰሙ ጥያቄ አዘል መፈክሮች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአልቡርሃን የሚመራው የሱዳን መንግስት ጥያቄዎችን ከማስተናገድና የህዝቡን የልበ ትርታ ከማድመጥ ይልቅ በጸጥታ መዋቅሩ አማካኝነት በሰልፈኞች ላይ የወሰደውና ያልተመጣጠነ ነው የተባለለት የኃይል እርምጃም በበርካታ ሱዳናውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗዋልም እየተባለ ነው።
የሰብዓዊ መብቶች እስከመጣስ በደረሰው የመንግስት እርምጃ የተቆጡ ሱዳናውያን፤ በትናትናው እለት ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ ሀገሪቱ ከተሞች ላይ የ”ክብራችን ይመለስ” ተቃውሞ እያሰሙ እንደዋሉም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
በመምህራን ማህበር እና ተቃውሞ በሚመራው ኮሚቴ እንደተጠራ በሚነገርለት የትናንትናው ሰልፍ፤ ባለፈው ሳምንት በደቡብ ዳርፉሯ ኒያላ ከተማ የተካሄደ ሰልፍን ተከትሎ ፖሊስ በንጹሃን ሰልፈኞች እና መምህራን ላይ የወሰደውን ያልተመጣጠነ እርምጃ ለማውገዝ የተደረገ ሰልፍ እንደነበርም ተገልጿል።
ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ከሆነ ትናንት በኦምዱርማን ግዘት ውስጥ በተካሄደው ሰልፍ ባቢከር አል-ራሺድ የተባለ ሰልፈኛ ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ደረቱ ተመቶ ሞቷል።
ባቢከር፤ የወርሃ ታህሳሱን ተቃውሞ ሲመራ በተመሳሳይ መንገድ የተገደለውን ባዳዊ አል-ራሺድ ወንድም መሆኑን ያስታወሰው የኮሚቴው መግለጫ፤ “ባቢከር አል-ራሺድ በሱዳናውያን ዘንዳ መቼም የማይዘነጋ ሰማዕት ነው” ሲልም ገልጾታል።
በትናትናው የተቃውሞ ሰልፍ በተለይም በካርቱም፣ ኦምርማን፣ ሴናር፣ማዳኒ፣ገደራፍ እና ባህሪ ከተሞች፤ የሱዳን ፖሊስ በሰልፈኞች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ አስለቃሽ ጋዝ ሲጠቀም እንደነበር የአይን እማኞች አል-ዐይን ተናግሯል።
በአልቡርሃን የሚመራው ወታዳረዊ ኃይል እንደፈረንጆቹ ጥቅምት 25 መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክን እና ካቢኔያቸውን ከስልጣን በማስወገድ በትረ ስለጣኑን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ ወዲህ፤ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገረ ሱዳን በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች።
የፖለቲካ ቀውሱን ተከትሎ እየተስተዋለ ያለው የኢኮኖሚ ቀወስም ሀገሪቱ ወደማያባራ ሁከት ውስጥ እንዳይከታት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል።
በዚህም አላቆመም፤ አሜሪካን ጨምሮ የአልቡርሃን ጀሮ ያላገኙ ሀገራት እና ተቋማት በሱዳን ላይ የተላያዩ ማዕቀቦች በመጣል ላይ ናቸው።
በትናንትናው እለት አሜሪካ በሱዳን ተጠባባቂ ኃይል ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ በድረ-ገጽ ላይ እንዳመላከተው ከሆነ፤ በተጠባባቂው የፖሊስ ኃይል ላይ ማዕቀብ ሊጣል የቻለው በሱዳን የተፈጠረውን አመጽ ተከትሎ “በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ እና በፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው” መሆኑን አስታውቋል።