ቭላድሚር ፑቲን፤ ከማሊ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት ጋር መወያየታቸውን ገለጹ
የሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ግንኙነት የአፍሪካና ሩሲያን ወዳጅነት ያጠናክራል ተብሏል
ምዕራባውያን፤ ሩሲያ በማሊ የምታደርገው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ሲገልጹ ነበር
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከማሊ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት ጋር መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ።
ቭላድሚር ፑቲንና የማሊው መሪ አሲሚ ጎይታ፤ በሁለትዮሽ ትብብር ማለትም በንግድ፣ በኢኮኖሚና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።
የማሊው መሪ አሲሚ ጎይታ፤ ሩሲያ ላደረገችላቸው ድጋፍ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ማመስገናቸውም ተሰምቷል።
መሪዎቹ፤ የሩስያ የምግብ፣ የማዳበሪያ እና የነዳጅ ምርቶች ወደ ማሊ መድረስ በሚችሉባቸው ነጥቦች ላይም መነጋገራቸው ተሰምቷል።
የሚመለከታቸው የሩሲያ እና የማሊ ተቋማት የሥራ ክፍሎች የሁለቱን ሀገራት ትብብር እንዲያጠናክሩ ስምምነት ተደርጓል ተብሏል።
መሪዎቹ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር ያለው የሩሲያ እና የማሊ የውጭ ግንኙነት ትብብር እንዳስደሰታቸውም ገልጸጸዋል ተብሏል።
የማሊው የሽግግር መንግስት መሪ አሲሚ ጎይታ በማሊ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋትና በአሸባሪ ቡድኖች እርምጃ ለመውሰድ የታቀደውን ዕቅድ ጨምሮ፤ በማሊ ውስጥ የተከናወኑ ስራዎችን ለፕሬዝዳንት ፑቲን ገልጸውላቸዋል ተብሏል።
ቭላድሚር ፑቲን ፤ እ.ኤ.አ. በ 2023 በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ሊካሄድ የታቀደው የሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከመላው አፍሪካ ሀገራት ጋር ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ምዕራባውያን ሀገራት፤ ሩሲያ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በነበረችው ማሊ ውስጥ የምታደርገው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱም እንዳሳሰባቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂን ይቭስ ሊ ድሪያን የካቲት ወር ላይ፤ በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄደው ወታደራዊ ኃይል “ሕገ ወጥ እና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የማሊ ወታደራዊ መሪዎች፤ በማሊ የነበሩት የፈረንሳይ አምባሳደር ጆል ሜየር በ 72 ሰዓት ውስጥ ከማሊ እንዲወጡ ማድረጋቸው ይታወሳል።