የሩሲያ ጦር ዓመታዊ ፎረም በሞስኮ አቅራቢያ ተጀምሯል
ወዳጆቿን ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ ዝግጁ መሆኗን ሩሲያ ገለጸች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ሃገራቸው ለወዳጆቿ ዘመናዊ ጦር መሳሪያዎችን ለማስታጠቅ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
በላቲን አሜሪካ፣ ኤሽያ እና አፍሪካ ከሚገኙ ሃገራት ጋር ላላቸው ግንኙነት ዋጋ እንደሚሰጡ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ሃገራቱን ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ ዝግጁ ነን ብለዋል በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በተላለፈ ንግግራቸው።
የሩሲያ ጦር ዓመታዊ ፎረም በሞስኮ አቅራቢያ ተጀምሯል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ በፎረሙ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግርም ነው ፑቲን ይህን ያሉት።
በንግግራቸው "ከቀላል እስከ ከባድ፤ ብረት ለበስ እና ሰው አልባ እጅግ ዘመናዊ ጦር መሳሪያዎችን ለወዳጆቻችን ለመስጠት ዝግጁ ነን" ብለዋል።
የሩሲያ መሣሪያዎች "በአስተማማኝነታቸው፣ በጥራታቸውና በሚሰጡት ጥቅም እንዲሁም ባላቸው ከፍተኛ ብቃት" በወታደራዊ ጠበብት ዘንድ ተመራጭ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።
"ሁሉም በሚባል ደረጃ ከአንድ ጊዜ በላይ በአውደ ውጊያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል" ሲሉም ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።
ሃገራቸው በዩክሬን በማካሄድ ላይ ካለችው ዘመቻ ጋር በተያያዘ በተገለለችበት በዚህ ወቅት ከጎኗ የቆሙ 'ብዙ' ወዳጆቿንም አመስግነዋል እንደ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ።
በተደራረቡ ማዕቀቦች እና እገዳዎች ስር ያለችው ሩሲያ በጦር መሳሪያ ሽያጭ ከአሜሪካ በመቀጠል ከዓለማችን ሁለተኛዋ ሃገር ናት።
ሆኖም እንደ ስቶኮልም ዓለምአቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም (SPIRI) መረጃ ከሆነ የምትሸጣቸው ጦር መሳሪያዎች መጠን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየቀነሰ መጥቷል።
ጦር መሳሪያ አምራቹ የሃገሪቱ መንግስት ተቋም (ሮስቴክ) ግን በዚህ አይስማማም። የተቋሙ ዋና አስተዳዳሪ ሰርጊ ኬሞዞቭ በፎረሙ እንደተናገሩት ከሆነ በዩክሬን በመካሄድ ላይ ያለው ዘመቻ የሩሲያን የጦር መሳሪያ ንግድ አላቀዛቀዘውም። በዚህ ዓመት ብቻ የአንድ ትሪሊዮን ሩብል ( 16 ቢሊዮን ዶላር ) ዋጋ ያላቸው የግዥ ስምምነቶችን ተፈራርመናልም ብለዋል።