በአዋጁም ወደ ሩሲያ የሚገቡ ዩክሬናዊያን 10 ሺህ ሩብል በየወሩ ይከፈላቸዋል ተብሏል
ሩሲያ ወደ ግዛቷ ለሚገቡ ዩክሬናዊያን ወርሀዊ ደመወዝ እንዲሰጣቸው አወጀች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ስድስት ወራት ሆኖታል።
በዚህ ጦርነት ሩሲያ 20 በመቶ የዩክሬን ግዛቶችን መቆጣጠሯን የገለጸች ሲሆን በሞስኮ ቁጥጥር ስር ያሉ ግዛቶችም ከቀናት በኋላ ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ በሂደት ላይ ናቸው።
ሩሲያ ወደ ግዛቷ ሊሚገቡ ዩክሬናዊያን የሩሲያ ዜግነት እና ፓስፖርት በመስጠት ላይ ትገኛለች።
አሁን ደግሞ ወደ ሩሲያ ለሚገቡ ዩክሬናዊያን ወርሀዊ ደመወዝ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአዲሱ አዋጅ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው የተገለጸ ሲሆን በዚህ አዋጅ መሰርትም ወደ ሩሲያ የሚገቡ ዩክሬናዊያን 10 ሺህ ሩብል ወይም 170 ዶላር በየወሩ ይከፈላቸዋል ተብሏል።
ዩክሬን የሩሲያን ድርጊት በሉዓላዊነቴ ላይ የተቃጣ ሌላኛው አደጋ መሆኑን ጠቅሳ ተቃውማለች።
ዩክሬን ከሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ወታደራዊ ጥቃት ለመቀልበስ በአሜሪካ እና ምዕራባዊያን አጋሮቿ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እየተደረገላት ይገኛል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያ ጋር ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ላለችው ዩክሬን ተጨማሪ የሶስት ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ፈርመዋል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 186ኛ ቀኑ ላይ ሲገኝ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።