የሩሲያው ፕሬዝደንት ባካሄዱት የካቢኔ የስልጣን ሽግሽግ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን ሰሬጌ ሾይጉን ተክተዋቸዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አምስተኛ ዙር የስልጣን ዘመናቸውን ከጀመሩ በኋላ ባካሄዱት የካቢኔ የስልጣን ሽግሽግ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን ሰሬጌ ሾይጉን ተክተዋቸዋል።
በሩሲያ ህግ በመሰረት፣ፕሬዝደንት ፑቲን በክሬሚሊን በዓለ ሲመት ከፈጸሙ በኋላ ሁሉም የካቢኔ አባት ባለፈው ማክሰኞ እለት ኃላፊነታቸውን ለቀዋል። አብዛኞቹ የካቢኔ አባላት በኃላፊነት እንደሚቀጥሉ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን የሾይጉ እጣፈንታ ግን አልታወቀም ነበር።
ፕሬዝደንት ፑቲን ሰርጌ ሾይጉን የሩሲያ የደህንነት ምክርቤት ሃላፊ አድርገው መሾማቸውን ክሬሚሊን ገልጿል።
ሹመቱ ይፋ የሆነው ፑቲን አንድሬ ቤሎሶቭ በሾይጉ ቦታ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስተር እንዲሆኑ ካቀረቡ በኋላ ነው።
የሾይጉ አዲሱ ሹመት ይፋ የሆነው የሩሲያ ባለስልጣናት ዩክሬን አድርሳዋለች በሚሉት ጥቃት በድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የቤልጎሮድ ከተማ 13 ሰዎች መገደላቸውን እና 20 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል።
የቤሎሶቭ ሹመት በሩሲያ ፓርላማ ቀርቦ መጽደቅ ይኖርበታል።
ፕሬዝደንት ፑቲን ሌሎች የካቢኔ አባላት በድጋሚ በያዙት ቦታ እንዲቀጥሉ ሲያደርጉ ሾይጉ ብቻ እንዲተኩ ተደርገዋል ተብሏል።
የሾይጉ ምክትል የሆኑት ፒሙር ኢቫኖቭ ባለፈው ወር ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ። የኢቫኖቭ መታሰር ለፑቲን ቀኝ እጅ በሆኑት ሾይጉ ላይ የተቃጣ ጥቃት አድርገው የወሰዱትም ነበሩ።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደች ያለውን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" በተለይም በምስራቅ ዩክሬን አጠናክራ ቀጥላለች።
ሩሲያ በከፊል የያዘቻቸውን አራት የዩክሬን ግዛቶች ሙሉ በሙሉ ሳትጠቀልል ዘመቻዋን እንደማታቆም ደጋግማ ገልጻልች። በድንበር የሚገኙ ግዛቶችን ከጥቃት ለመከላከል፣ በዩክሬን ግዛት ውስጥ ከጦርነት ነጻ ቀጠና እንደሚያስፈልጋት በመግለጽ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬኗ የካርኪቭ ግዛት አምስት መንደሮችን መቆጣጠሯን አስታውቃለች።