የሩሲያ መከላከያ ሰራዊት በበኩሉ የዋግነር ተዋጊዎች ትጥቃቸውን እየፈቱ እንደሆነ ገልጿል
የዋግነሩ አዛዥ የቨግኒ ፕሪጎዚን ጦሩን የመምራት ፍላጎት እንደሌላቸው ተገለጸ።
የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ዋግነር የሩሲያ ወታደሮች ጥቃት ከፈቱብኝ በሚል ከሶስት ሳምንት በፊት የአጸፋ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል።
የቡድኑ አዛዥ የቨግኒ ፕሪጎዚንም በሩሲያ ጦር ላይ የጀመሩትን ጥቃት የከፋ ደም እንዳይፈስ በሚል ውጊያ ማቆማቸውን በወቅቱ ገልጸውም ነበር።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በየቨግኒ ፕሪጎዚን ላይ ከፍተውት የነበረውን የሀገር ክህደት ክስ ውድቅ ሲያደርጉ የቨግኒ ፕሪጎዚንም ወደ ቤላሩስ ማምራታቸው ይታወሳል።
ይሁንና ፕሪጎዚን በቤላሩስ ይቆያሉ ተብሎ ቢጠበቅም ብዙም ሳይቆዩ ወደ ሩሲያ መመለሳቸው ብዙዎችን ማስገረሙ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ፕሪጎዚን በሞስኮ የፊት ለፊት ውይይት አድርገዋል የተባለ ሲሆን በውይይቱ ላይ ከሁለቱ በተጨማሪ የተወሰኑ የዋግነር ወታደሮችም ተሳትፈው ነበር ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ዋግነር ከሚፈርስ ይልቅ አሁንም ሩሲያን እንዲያገለግል ይፈልጋሉ የተባለ ሲሆን ፕሪጎዚንም ዋግነርን እንዲመሩ ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
ይሁንና የቨግኒ ፕሪጎዚን ዋግነርን የመምራት ፍላጎት እንደሌላለው ለፕሬዝዳንት ፑቲን በቀጥታ እንደነገራቸው የሩሲያ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለውም ዋግነር ህጋዊ ተቋም እንዳልሆነ ነገር ግን የሩሲያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል መቋቋሙን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለውም የዋግነር አባላት ተዋጊዎች ሀገራቸው ከዩክሬን ጋር እያደረገች ባለው የውጊያ ግንባር መዋጋት አቁመዋል ብለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን የሩሲያ መከላከያ ሰራዊት የዋግነር ተዋጊዎች ትጥቃቸውን እየፈቱ እንደሆነ ገልጿል።