
ከጦርነቱ ወዲህ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች ከዩክሬን መሰደዳቸው ተገልጿል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦራቸው ላይ ንጹሃን እንዳይጎዱ “የሚችለውን ሁሉ” እያደረገ መሆኑን ገለጹ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ከአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው ተብሏል፡፡ ሁለቱ ወገኖች በስልክ ያደረጉት ንግግር ወቅታዊውን የዩክሬን ጉዳይ የተመለከተ መሆኑን ክሬምሊን አስታውቋል፡፡
የሩሲያ ጦር፤ በዩክሬን የሚገኙ ንጹሃን እንዳይጎዱ እየሰራ እንደሆነም ፑቲን ለቻርለስ ሚሼል ገልጸውላቸዋል ነው የተባለው፡፡ የዩክሬን ጦር ንጹሃንን እንደመደበቂያ እየተጠቀመ መሆኑን የተናገሩት ቭላድሚር ፑቲን፤ የአውሮፓ ሕብረት ንጹሃንን በማዳኑ በኩል “እውነተኛ” አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሕብረቱ የዩክሬን ባለስልጣናት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ እንዲያከብሩ ጫና ማድረግ እንዳለበት የገለጹት ፑቲን የንጹሃንን ህይወት ማትረፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ከአውሮፓ ሕብረት ፕሬዝዳንት በተጨማሪም ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ጋር ውይይት አድርገዋል ተብሏል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ባደረጉት ንግግር ፑቲን ፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕንዳውያንን ለማስወጣት የሩሲያ ጦር “ጥሩ” ስራ እየሰራ እንደሆነ ለናሬንድራ ሞዲ ገልጸውላቸዋል ተብሏል፡፡
የሕንድ ተማሪዎች በካርኪቭ እንደማስያዣ ተደርገው የነበረ ቢሆንም በኪቭ ላይ ዓለም አቀፍ ጫና ሲደረግ እንደተለቀቁም ነው በሁለቱ መሪዎች ውይይት የተነሳው፡፡ የሕንድ ዜጎች ከጦርነት ቀጠና እንዲወጡ በመደረጉ ናሬንዲራሞዲ፤ ቭላድሚር ፑቲንን አመስግነዋል ተብሏል፡፡
ዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ አንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች መሰደዳቸው በተመድ ይፋ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከጦርነቱ ወዲህ በዩክሬን 406 ንጹሃን ሲገደሉ፤ 801 የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡