የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት የሩሲያ ጉብኝት ለምን ምዕራባውያንን አስቆጣ?
የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ዋንግ ይ በሞስኮ ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መክረዋል
ቤጂንግ በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ከሞስኮ ጎን ከተሰለፈች ሶስተኛው የአለም ጦርነት አይቀሬ ነው እየተባለ ነው
የምዕራባውያኑ እና የሩሲያ ፍጥጫ በየቀኑ እየጨመረ ይገኛል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በኬቭ ድንገተኛ ጉብኝት ባደረጉ ማግስት የቻይናው ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማት ዋንግ ይ ሞስኮ ደርሰዋል።
ዲፕሎማቱ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር መነጋገራቸውም ተገልጿል።
በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ቻይና የያዘችው አቋምን ሲቃወሙ የቆዩት ምዕራባውያን የዋንግ ይን ጉብኝት በበጎ አልተመለከቱትም።
ቤጂንግ ለሞስኮ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ልታደርግ ተዘጋጅታለች የሚሉ ወቀሳዎችን የሚያጠናክር አድርገውም እያቀረቡት ነው።
ዋንግ ከውይይቱ በኋላ፥ የሩሲያ እና ቻይና ትብብር “ምንም አይነት ገደብ የለውም” ማለታቸውም ስጋታቸው እንዲያይል አድርጎታል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭም “አለም አቀፍ ረብሻው ቢቀጥልም ትብብራችን በአስገራሚ ፍጥነት ቀጥሏል” ሲሉ መደመጣቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ፥ ቻይና ለሩሲያ የጦር መሳሪያ የምትደግፍ ከሆነ ሶስተኛው የአለም ጦርነት በይፋ ይጀመራል የሚል ስጋታቸውን ማንሳታቸው የሚታወስ ነው።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም፥ ቤጂንግ የክሬምሊንን የዩክሬን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በየትኛውም መንገድ ካገዘች “አደገኛ ችግር” ይፈጠራል ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
በምዕራባውያን የማዕቀብ ጫና የተጎዱት ቻይና እና ሩሲያ ግን ለምዕራባውያኑ ዛቻ ቁብ ሳይሰጡ ትብብራቸውን ማጠናከር ላይ የተጠመዱ ይመስላል።
ሀገራቱ በተለያየ ጊዜ ያደረጓቸው የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችም አሰላለፋቸውን በግልጽ ያሳየ ነው በሚል በምዕራባውያኑ ይነሳል።
የቻይናው የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኮሚዩኒስት ፓርቲው የውጭ ጉዳዮች ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ይ ትናንት ከሩሲያ ብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ጸሃፊ ኒኮላይ ፓትሩሼቭ ጋር መምከራቸውም ይህንኑ ስጋር አንሮታል።
ፓትሩሼቭ በዚህ ውይይት ላይ ምዕራባውያኑ የቻይና እና ሩሲያን ግንኙነት በማሻከር የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት እናከሽፋለን ሲሉ ተደምጠዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለስንኪ ወደ አሜሪካ በሚስጢር ሲጓዙ፥ የሩሲያ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበሩ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ወደ ቤጂንግ ማቅናታቸው ይታወሳል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኬቭ በደረሱ ማግስት ደግሞ የቻይናው ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማት ሞስኮ ገብተዋል።
ይህ ቀላል ግጥምጥሞሽ አይደለም የሚሉ ተንታኞች ሃያላኑ የዩክሬን ምድርን የጦርነት አውድማ ከማድረግ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ውጥረቱን እንዲያረግቡት ይመክራሉ።