ከሩሲያ ጎን ያልቆሙ ሀገራት ጋዝን ለመግዛት በሩሲያ ባንኮች አካውንት መክፈት አለባቸው ተብሏል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ከነገ ጀምሮ ጋዝ በራሷ የመገበያያ ገንዘብ “ሩብል” እንዲሸጥ በቀረበው ሰነድ ላይ መፈረማቸው ተገለጸ።
ፕሬዝዳንቱ ወደ አውሮፓ የሚደረገው የጋዝ ሽያጭ በሩሲያ ገንዘብ እንዲሆን ቀደም ሲል ውሳኔ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ሞስኮ ጋዝን በራሷ የመገበያያ ገንዘብ ሩብል እንዲሸጥ የወሰነችው ከጎኗ ላልቆሙ ሀገራት መሆኑን የሩሲያው አርቲ ዘግቧል።
ሩሲያ ጋዝን በራሷ ገንዘብ መሸት የምትጀምረው ከነገ ጀምሮ መሆኑን የገለጹት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ ቀደም ዶላር “የሚታመን መገበያያ” እንልዳሆነ ገልፀው ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቱ የፈረሙት ሰንድ አሁን ላይ ከሩሲያ ጎን ያልቆሙ ሀገራት ጋዝን ለመግዛት በሩሲያ ባንኮች አካውንት መክፈት እንዳለባቸው እንደሚያስገድድም ነው የተገለጸው።
ሞስኮ ከዚህ በኋላ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ጋር በዩሮም ሆነ በዶላር የመገበያየት ስሜት እንደሌላት የሩሲያ ባለስልጣናት መግለጻቸው ይታወሳል።
ሩሲያ፤ ወዳጅ ያልሆኑ ሀገራት ያስቀመጠችውን ቅድመ ሁኔታ ካላሟሉ ጋዝ የመሸጥ ውሉን እንደምታቆም አስታውቃለች። ከዚህ የሩሲያ ውሳኔ በኋላ ጀርመን እና ፈረንሳይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስቴር ፓሪስ እና በርሊን ሩሲያ ያስቀመጠችውን ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀበሉት ገልጿል፡፡
አሜሪካ፤ የሩሲያ ነዳጅ ወደ ሃገሯ እንዳይገባ መከልከሏ የሚታወስ ሲሆን የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች ደግሞ የሩሲያ ነዳጅ አሁን ላይ በገበያው ላይ እንደሚያስፈልግ ገልጻለች።
የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ እና የካቢኔ አባላት ከአውሮፓ ጋር በሩብል የሚካሄደውን ግብይት በተመለከተ በአንድ ሳምንት ውስጥ ውሳኔ እንዲያስቀምጡ ፑቲን ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
ሩሲያ ቀደም ሲል ምዕራባዊያንን እንደምትጎዳቸው ማስጠንቀቂያ ስትሰጥ ቆይታለች። የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ክምችት መቀነሱንና ፍላጎት ደግሞ በአራት ሚሊዮን በርሜል መጨመሩን ገልጸው ነበር።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ)፤ በሩሲያ ላይ የተጣሉ የገንዘብ ማዕቀቦች የዶላርን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሊቀንሱት እንደሚችሉ ገልጿል።
የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጊታ ጎፒናዝ አሁን ላይ አሜሪካን ጨምሮ የተለያያ ወገኖች በሞስኮ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች የዓለምን የገንዘብ ሥርዓት የተበታተነ ሊያርገው እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።