በአውሮፓ በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪና ንግድ እየደራ ነው ተባለ
ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ለዩክሬን ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ እርዳታ ሰጥተዋል
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ለክልሉ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪ አዳዲስ እድሎችን መፍጠሩ ተናግሯል
የምስራቅ አውሮፓ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ዩክሬን ሩሲያን ለመዋጋት በምታደርገው ጥረት መድራቱ ተነግሯል።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪው ማደጉ የተነገረ ሲሆን፤ ሽጉጥ፣ መድፍ እና ሌሎች ወታደራዊ አቅርቦቶችን በብዛት እየተቸበቸቡ ነው ተብሏል።
ሮይተርስ እንደዘገበው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የኪየቭ አጋሮች የየራሳቸውን ምርቶች በማሟጠጥ የጦር መሳሪያዎችን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እያቀረቡ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ ከጥር እስከ ጥቅምት ባሉት አስር ወራት ውስጥ ለዩክሬን ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ እርዳታ ሰጥተዋል። ፖላንድ በመከተል በሦስተኛ ደረጃ የዩክሬት የጦር መሳሪያ አቅራቢ ስትሆን፤ ቼክ ሪፐብሊክ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ተብሏል።
የቀድሞ የዋርሶ ስምምነት ሀገራት ዩክሬንን መርዳት እንደ ክልላዊ ደህንነት ጉዳይ አድርገው እንደሚመለከቱት ተገልጿል።
ሮይተርስ ያነጋገራቸው በርካታ የመንግስት እና የኩባንያ ኃላፊዎች እና ተንታኞች ግጭቱ ለክልሉ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪ አዳዲስ እድሎችን መፍጠሩን ተናግረዋል።
የፖላንድ መሳሪያ አምራች በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ እስከ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ስለማቀዱ ተናግሯል።
ይህም ከጦርነቱ በፊት ከታቀደው በእጥፍ ይበልጣል ተብሏል።
ሩሲያ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ አንዳንድ የምስራቅ አውሮፓ ወታደሮች እና መሳሪያ አምራቾች የሶቪየት ዘመን የጦር መሳሪያዎች እና የጥይት ጎተራዎቻቸውን ባዶ ማድረግ ጀምረዋል።
ኪየቭ ከምዕራቡ ዓለም የኔቶን ደረጃውን የጠበቀ መሳሪያ እየጠበቀች ነበር።