ፑቲን “የዩክሬን ጦርነት ዓለም አቀፋዊ እየሆነ ነው” አሉ
ፑቲን “መሳሪያዎቻቸው የእኛን ተቋማት እንዲመቱ በሚፈቅዱት ሀገራት ወታደራዊ ተቋማትን ለማምታት እያጤንን” ብለዋል
ሩሲያ በሰከንድ 3 ኪ.ሜ የሚከንፍ አዲስ የመካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል በመጠቀም ዩክሬንን መምታቷን አረጋግጠዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላደሚር ፑቲን ሀገራቸው ከዩክሬን ጋር የገጠመችው ጦርነት ዓለም አቀፋዊ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላደሚር ፑቲን በትናንት ምሽቱ ንግግራቸው፤ አሜሪካ እና ብሪታኒያ ዩክሬን የረጅም ርቀት መሳሪያዎቻቸውን ተጠቅማ ሩሲያን እንድታጠቃ መፍቀዳቸውን ተከትሎ ጦርነቱ ወደ አለም አቀፍ ግጭት እየተሸጋገረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ፑቲን በንግግራቸው የአሜሪካ እና የብሪታኒያ ሚሳዔሎች ሩሲያን ለማጥቃት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተከትሎ ሞስኮ አዲስ የመካከለኛ ርቀት ሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል በዩክሬን ወታደራዊ ተቋም ላይ በመተኮስ የአጸፈ ምላሽ ሰጥታለች ብለዋል።
“ተጨማሪ የአጸፋ እርምዎችም ይከተላሉ” ሲሉ ያስጠነቀቁት ፑቲን፤ ሩሲያ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እንደምትሰጥም አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለውም፤ “አሜሪካ በፈረንጆቹ 2019 የተፈረመውን የሚሳዔል ስምምነት በመጣስ ትልቅ ስህተት ሰርታለች” ሲሉም ተናግረዋል።
“አሜሪካ የዓለም ሀገራትን ወደ ዓለም አቀፍ ግጭት እየገፋች ነው” ሲሉም ፕሬዝዳንት ፑቲን በንግግራቸው አሳስበዋል።
ፑቲን ለምእራባውያን ሀገራትም የማስጠንቀቂያ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ “ማንኛውም ጠብ አጫሪ እንቅስቀሴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን” በማለት ዝተዋል።
ዩክሬን ሩሲያን ለማጥቃት የአሜሪካ እና የብሪታኒያ የረጅም ርቀት ሚሳዔሎችን መጠቀሟን ያረጋገጡት ፑቲን፤ የጦር መሳሪያዎቹ በጦር ሜዳ ያለውን ጨዋታ አይቀይሩም፤ ሩሲያ ወታደሮች አሁንም ወደፊት እየገፉ ነው ብለዋል።
ፑቲን በንግግራቸው “አሁን ላይ ዩክሬን መሳሪያዎቻቸውን ተጠቅማ በሩሲያ ተቋማት ላይ ጥቃት እንድትፈጽም የፈቀዱ ምእራባውያን ሀገራት ወታራዊ ተቋማት ላይ መሳሪያዎቻችንን ተጠቅመን እርምጃ የመውሰድ መብት እንዳለን እያጤንን ነው” ብለዋል።
“ይህንን የሚጠራጠሩ ካሉ ተሳስተዋል፤ ለሚፈጸም ማንኛውም ጥቅታ ሁልጊዝም መልስ አለ” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በትናነትናው ምሽት ንግግራቸው፤ ሀገራቸው የዩክሬኗ ዲኒፕሮን ያጠቃችው 'አዲስ ሚሳኤል' በመጠቀም መሆንን በማረጋገጥ ምዕራባውያንን አስጠንቅቀዋል።
ሚሳዔሉ በሰከንድ ከ2.5 እስከ 3 ኪሎ ሜትር የሚከንፍ ሲሆን፤ እስከ 5 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ኢላማ መምታት የሚችል ነው።
የሩሲያው ፕሬዝዳንቱ ቭላድሚር ፑቲን ባሳለፍነው ማክሰኞ የተሻሻለውንና የሩሲያን የኒዩክሌር መሳሪያ አጠቃቀም የሚወስነው ህግ ማጽደቃቸው ይታወሳል።
ሩሲያ በ2020 በይፋ ያወጣችውን የኒዩክሌር ህግ ማሻሻሏን ስትገልጽ የቆየች ሲሆን፥ ባይደን ለኬቭ ይሁንታ በሰጡ ማግስት ነው ፑቲን ማሻሻያውን ያፀደቁት።
ማሻሻያው ኒዩክሌር ያልታጠቁ ሀገራት ከታጠቁት ጋር በመተባበር በሩሲያ ላይ ጥቃት ካደረሱ በሞስኮ ላይ “የጋራ ጥቃት” እንደከፈቱ ይቆጠራል የሚል ሃሳብ አካቷል።
ሩሲያ የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን መቼ መጠቀም እንዳለባት በግልጽ የሰፈረበት ህግ፥ ድንበር አቋራጭ የሚሳኤል፣ የአየር እና ድሮን ጥቃት ከተፈጸመባት አውዳሚዎቹን መሳሪያዎች መጠቀም እንደምትጀምር የሚፈቅድ ነው።