ባለፉት ሶስት አመታት የግጭት ቀጠናዎች በሁለት ሶስተኛ መጨመራቸው ተገለጸ
ከ2021 ጀምሮ በጦርነት የተዋጠው የአለም ክፍል የህንድን የቆዳ ስፋት ሁለት እጥፍ እንደሚሸፍን ነው የተነገረው
4.6 በመቶ የሚሆነው የአለም መሬት ግጭት እየተካሄደበት ይገኛል ተብሏል
ባለፉት ሶስት አመታት የግጭት ቀጠናዎች በሁለት ሶስተኛ መጨመራቸውን ጥናት አመላከተ፡፡
ዩክሬን፣ ማያናማር፣ መካከለኛው ምስራቅ ፣ በአፍሪካ የሳህል ቀጠና ዙሪያ ያለው “የግጭት ኮሪደር” እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ከ2021 ጀምሮ ጦርነት እና አለመረጋጋት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡
ቬርሲክ ማብልክሮፍት የተባለው የግጭት መጠን ጠቋሚ ሪፖርቶችን የሚያወጣው ተቋም በነዚህ አመታት ግጭት የተከሰተባቸው ስፍራዎች ስፍፋይ የህንድን ሁለት እጥፍ እንደሚሸፍን ገልጿል፡፡
በሪፖርቱ መሰረት 6.15 ሚሊየን ስኩዌር ኪሎ ሜትር በሀገራት መካከል በሚደረግ ጦርነት የተሸፈነ ነው፤ ይህም ማለት 4.6 በመቶ የሚሆነው የአለም መሬት ግጭት እየተካሄደበት ይገኛል እንደማለት ነው፡፡
በ2021 2.8 በመቶ የምድር ክፍል ብቻ ግጭት ሲካሄድበት የነበረ ሲሆን ከዘንድሮው ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት ነው ተብሏል፡፡
ኢኳዶር፣ ኮሎምቢያ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዥያ እና ታይላንድን ጨምሮ በአጠቃላይ በ27 ሀገሮች ከ2021 ጀምሮ በግጭት የሚሞቱ የሰዎች ቁጥር በ29 በመቶ ከፍ ብሏል።
ሪፖርቱ ከማሊ እስከ ሶማሊያ ያለውን የሳህል እና የአፍሪካ ቀንድ የሚሸፍን የግጭት ኮሪደር የለየ ሲሆን በነዚህ አመታት ግጭት እና ብጥብጥ በሶስት በእጥፍ መጨመሩን ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት 86 በመቶ የቡርኪናፋሶ ክፍል በግጭት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሱዳን እና ኢትዮጵያም ከ2021 ጀምሮ መጠነ ሰፊ የሆነ ብጥብጥ እንደተከሰተባቸው አመላክቷል፡፡
ዩክሬን፣ ሱዳን፣ ጋዛ እና ሊባኖስን ጨምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ 470 ሚሊየን ህጻናት በጦርነት አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት ተጠቂ ሆነዋል፡፡
ህጻናቱ ወላጆቻቸውን በጦርነቱ ማጣታቸውን ተከትሎ ለጉልበት ብዝበዛ እና ወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ስለመሆናቸውም ነው የተነሳው፡፡
ከሰብአዊ ኪሳራ ባለፈ የቅርብ ጊዜ ግጭቶች በንግድ ፣ በኢኮኖሚ እድገት እና በምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል ፡፡
በሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የአቅርቦት ሰንሰለት እክል ገጥሞታል፤ ይህም የእህል ምርቶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ በበቂ አቅርቦት እንዳይላኩ አድርጓል፡፡
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነትን ተከትሎ ደግሞ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በንግድ መርከቦች ላይ ከየመን የሁቲ አማፅያን የሚደርሰው ጥቃት የንግድ ስርአቱ እንዲስተጓጎል ምክንያት ሆኗል፡፡