ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ተወያይተዋል
ደቡብ አፍሪካ ሩሲያ እና ዩክሬንን እንድታሸማግል መጠየቋን ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ተናገሩ፡፡
ራማፎዛ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱ ጦርነቱ በራሳቸው አቅም በሽምግልና እና ድርድር መቋጫ ሊያገኝ እንደሚገባ፤ ካስፈለገም ደግሞ ሌሎች አካላት ሊያግዙ እንደሚችሉ ለፕሬዝዳንት ፑቲን መግለጻቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለሃገራቱ የሚበጀው ይኸው አካሄድ እንደሆነም ነው ራማፎዛ የገለጹት፡፡
ይሄን ማለታቸውንና ደቡብ አፍሪካ በጉዳዩ ሚዛናዊ ቀረቤታን ማሳየቷን ፑቲን ማድነቃቸውንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ደቡብ አፍሪካ እና ሩሲያ የብሪክስ አባል ሃገራት ናቸው፡፡ ቻይና፣ ብራዚል እና ህንድንም ያካትታል፡፡ በዚህ ግንኙነታቸው ደቡብ አፍሪካ ሩሲያ እና ዩክሬንን እንድታሸማግል መጠየቋንም ነው ፕሬዝዳንቱ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ያስታወቁት፡፡ ሆኖም ጠያቂው ማን እንደሆነ አልገለጹም፡፡ ከሞስኮም ሆነ ከኪቭ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተሰጠ መረጃ የለም፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ከጀመረች 15 ገደማ ቀናት እየተቃረቡ ነው፡፡ ጦርነቱን በውይይትና ድርድር ለማቆም የጠለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ነው፡፡ ትናንት ሃሙስም በደቡባዊ ቱርክ አንታልያ ከተማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ተገናኝተው ለመወያየት ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ውይይቱን በስምምነት ለመቋጨት አልቻሉም፡፡