የራሽፎርድ የጎል ድርቅ በተሰበረበት ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ 3ለ0 አሸነፈ
በሊጉ ጅማሮ ተደጋጋሚ ሽንፈትን ያስተናገደው ዩናይትድ ሳውዝሀምፕተንን ማሸነፍ ችሏል
በተደጋጋሚ ጉዳቶች በአቋም መውረድ ሲተች የነበረው አጥቂው ማርከስ ራሽፎርድ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል
በውጤት ማጣት ትችትን ሲያስተናግድ የቆየው ማንችስተር ዩናይትድ በአመቱ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡
ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ከሳውዝ ሀምፕተን ጋር ዛሬ ከሰአት በኋላ ባደረገው ጨዋታ 3 ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡
በጫና ውስጥ የሚገኙት አሰልጣኝ ኤርክ ቴንሀግ በቅዱሳኖቹ ሜዳ ከነበረባቸው ውጥረት እረፍት የሚወስዱበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በሊጉ 6 ነጥቦችን በመያዝ 8ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።
ባሳለፍነው የውድድር አመት በታሪኩ መጥፎ የሚባለውን የውድድር ዘመን ያሳለፈው ዩናይትድ ሊጉ ከተጀመረ በኋላ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን ተሸንፏል፡፡
ቀያይ ሰይጣኖቹን ከቅዱሳኑ ጋር ባገናኘው የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ አራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር አንድሬ ኦናና ፍፁም ቅጣት ምት ሲያድን በራሽፎርድ ሁለት ጎሎች እና በአዲሱ ፈራሚ ማቲያስ ዲላይት ጎል ታግዞ ነው ዩናይትድ ያሸነፈው ።
በ33ኛው ደቂቃ ላይ የማንችስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ዳሎት በሰራው ጥፋት ሳውዝሀፕተኖች የፍጹም ቅጣት ምት ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡
ከሊቨርፑል ሽንፈት በኋላ ውጥረት ውስጥ የነበሩት አሰልጣኙ ኤሪክ ቴንሀግ የዚህ ጨዋታ ውጤት በቀጣይ በቡድኑ የሚኖራቸውን እጣ ፈንታ ሊወስን እንደሚችል ከጫዋታው በፊት የእንግሊዝ ጋዜጦች ጽፈዋል፡፡
አሰልጣኙ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት አስተያየት መጀመርያ አካባቢ የነበረን እንቅስቃሴ ደካማ ነበር፤ የፍጽም ቅታት ምት ከተሰጠብን በኋላ ተጨዋቾቼ ያደረጉት እንቅስቃሴ ጨዋታውን በበላይነት አሸንፈን እንድንወጣ አስችሎናል ብለዋል፡፡
የራሽፎርድን ግብ ማስቆጠር በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ተጫዋቹ ከተደጋጋሚ ጉዳቶች መልስ እራሱን ለማሻሻል ጠንካራ ልምዶችን ሲያደርግ መሰነበቱን አንስተው በቀጣይ ጨዋታዎች ቡድኑ የሚጠብቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ እንደሚቀጥል እምነት አለኝ ነው ያሉት፡፡
ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ማርከስ ራሽፎርድ በአቋሙ ላይ ትችት እየሰነዘሩ ለሚገኙ አካላት ዋሳኝ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር መልስ ሰጥቷል።
በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ በጋሬዝ ሳውዝ ጌት ስብስብ ውስጥ ያለተካተተው የ26 አመቱ አጥቂ በአቋሙ መውረድ ዙርያ የተለያዩ ጫና እና ትችቶችን እያስተናገደ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዛሬው እለት ማንችስተር ሲቲ ከብሬንትሮርድ ፣ ሊቨርፑል ከኖቲንግሃም እያደረጓቸው ያሉ ጫወታዎች ተጠባቂ ናቸው ።
የሳምንቱ ተጠባቂ የሰሜን ለንደን ደርቢ ጫወታ ነገ በዋይትህርትሌን ቶተንሃም ከአርሰናል ከቀኑ 10 ሰአት የሚያደርጉት ጫወታ ይጠበቃል ።