ብሪታንያ 18 ዓመት የሞላቸው ዜጎች በብሔራዊ ውትድርና እንዲያገለግሉ የሚያስገድድ ፖሊሲ ተግባራዊ ልታደርግ ነው
የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በመጭው ሰኔ በሚደረገው ምርጫ የሚመረጡ ከሆነ ፖሊሲው ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል

ብሪታንያ የብሔራዊ ውትድራና ፖሊስ ለወጣቶች ሁለት አማራጮች ይቀርባል ተብሏል
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚንስትር ሪሽ ሱናክ 18 አመት የሞላቸው ወጣቶች በብሔራዊ ውትድርና ለአንድ አመት እንዲያገለግሉ የሚያስገድድ ፖሊሲ አስተዋውቀዋል።
በፖሊሲው ለወጣቶች ሁለት አማራጮች የቀረቡ ሲሆን በብሔራዊ ውትድርና ማገለገል እና ለአንድ አመት በወር አንድ ግዜ ለአንድ ሳምንት ማህበራዊ አገልግሎትን መስጠት ናቸው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ፖሊሲው የጋራ ማህበረሰባዊ እሳቤ ለመፍጠር እና የጋራ አላማን ለማስረጽ ይረዳል ብለዋል።
ወጣቶች ከቀረቡላቸው ምርጫ በብሄራዊ ውትድርና ለአንድ አመት ማገልገልን ካልመረጡ በበጎ ፈቃድ ይሳተፉባቸዋል የተባሉ ተግባራት ተዘርዝረዋል።
እነርሱም በፖሊስ እና የእሳት አደጋ መስርያቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በአረጋዊያን ማቆያዎች ውስጥ ማህበራዊ አገልግሎቶችን መስጠት ናቸው።
የወግ አጥባቂ ፓርቲ ዋነኛ ተቀናቃኝ ፓርቲ የሆነው የሌበር ፓርት እጩው ሰር ኪር ስታርመር ፍርያማ የማይሆን በወጉ ያልተጠና እቅድ በሚል ፖሊሲውን አጣጥለዋል።
እሳቸው በአለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣውን የደህንነት ስጋት ለመከላከል መፍትሄው ወታደራዊ አቅም ማሳደግ ነው ባይ ናቸው።
የወግ አጥባቂ ፓርቲው’’ በአለም ላይ የሚፈራውን ጦራችንን ቁጥሩን በመቀነስ እና በጀቱን በማሳነስ ለስጋት እየዳረገን ነው ብለዋል። ይህ ፖሊሲ ደግሞ የሀገሪቷን ለተጨማሪ ወጭ የሚዳረግ ረብ የለሽ ሀሳብ ነው’’ ሲሉ ነቀፌታቸውን ሰንዝረዋል።
ሱናክ በበኩላቸው ይህ ፖሊስ ወጣቶች በሀገራቸው ጉዳይ ያገበናል እንዲሉ ማህበረሰባዊ አገልግሎትን ይማሩ ዘንድ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ያምናሉ።
ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ ከወታደሩ እና ከዜጎች የተውጣጡ አባላት የተካተቱበት ኮሚሽን እነደሚቋቋም ይፋ አድርገዋል፡፡ ኮሚሽኑ በብሄራዊ አገልግሎቱ የሚካተቱ ተግባራት እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሚወስን ነው።
ምዝገባው በሚቀጥለው አመት መስከረም ላይ የሚጀምር ሲሆን አጠቃላይ የፖሊሲው ትግበራ በአመት 2.5 ቢልዮን ፓውንድ እንደሚያስወጣ ነው የተነገረው።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቬድ ካሜሮን መሰል የብሄራዊ አገልግሎት ፖሊስን ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ እስተዋውቀው የነበረ ቢሆንም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።