ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት ከሩሲያ ጋር በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት መስማማታቸው ተገለጸ
ሀገራቱ በማዕከላዊ ባንኮቻቸው በኩል ገንዘቦችን በመለዋዋጥ በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ነው የተስማሙት

ሞስኮ በብሪክስ በኩል አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዷን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ የ100 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ገቢራዊ እንደሚያደርጉ ዝተዋል
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከናይጄሪያ እና ቱኒዝያ ከሩሲያ ጋር በሀገር ውስጥ ገንዘብ ለመገበያየት ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።
የዩክሬኑን ጦርነት ተከትሎ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ከዶላር ውጭ የሆነ ግብይት ለመፈጸም ስምምነቶችን እያደረገች የምትገኝው ሞስኮ ተጨማሪ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን አካታለች፡፡
ከክሪምሊን የወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው ይህን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር በሀገር ውስጥ ገንዘብ ለመገበያየት ስምምነት ላይ የደረሱ ሀገራት ቁጥር 40 ደርሷል፡፡
እንደ አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በመስከረም 2023 በሩሲያ መንግስት የጸደቀው የመጀመሪያው ዝርዝር ውስጥ ነበሩ።
የአርጀንቲና፣ የካምቦዲያ፣ የላኦስ፣ የሜክሲኮ፣ የናይጄሪያ፣ የቱኒዚያ እና የኢትዮጵያ የንግድ ተወካዮች በመገበያያ ገንዘብ ንግድ እንዲሰማሩ አዲስ ፈቃድ አግኝተዋል፡፡
የሩሲያ መንግስት መመሪያው የሩስያ ኢኮኖሚን በመገበያያ ገንዘብ የሚከፍለውን ፍላጎት ለማሟላት እና ወዳጃዊ እና ገለልተኛ መንግስታት ብሔራዊ ገንዘቦችን በቀጥታ በመለዋወጥ የስርዓቱን ውጤታማነት እንደሚያሳድግ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሀገራቱ ከሩሲያ ጋር በሚፈጽሙት ግብይት የሚያጋጥማቸውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ እና የተሸለ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ግዛል ተብሏል፡፡
ስፑትኒክ በዘገባው ጦርነቱን ተከትሎ በምዕራባውን ሀገራት እየተጠናከረ የሚገኘውን ማዕቀብ ጫና ለመቋቋም የሩሲያ መንግስት አማራጭ የመገበያያ መንገዶችን በማፈላለግ ላይ ይገኛል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት በስዊፍት አለም አቀፍ የገንዘብ ማስተላለፍያ መንገድ ላይ ማዕቀብ ከተጣለበት በኋላ ጠንካራ የኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲያዊ አጋር እንደሆኑ ከሚነገርላቸው ቻይና እና ህንድ ጋር የሚፈጽመውን ግብይት በራሳቸው ገንዘብ ለማድረግ መስማማቱ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም የብሪክስ አባል ሀገራት ጠንካራ የፋይናንስ ተቋም እና ነጻ የግብይት ሰንሰለት ለመፍጠር ባስቀመጠው ዕቅድ የራሱን የመገበያያ ገንዘብ ማስተዋወቁ ይታወሳል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን ገንዘብ ተግባራዊ ማድረግ እና ዶላርን ከዋና የመገበያያ ገንዘብነት ለማስወጣት የሚደረግ ጥረት በሀገራት ላይ ማዕቀብ እና የ100 በመቶ ታሪፍ ጭማሪን ተግባራዊ እንደሚያስደርግ ዝተዋል፡፡