ሩሲያ በዩክሬን እየተፋለሙ ላሉ ወታደሮቿ “ልዩ መብቶች” ልትሰጥ ነው
ልዩ መብቶቹ ወታደሮች ግብርን ጨምሮ ሌሎች አግልግሎቶችን በቅናሽ ዋጋ ለማግኘት የሚያስችሉ ናቸው
የሩሲያ መንግስት ልዩ መብቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ 50 ሚልየን ዶላር መመደቡን ይፋ አስታውቋል
የሩሲያ ፓርላማ የሀገሪቱ መንግስት በዩክሬን ላይ እየተዋጉ ላሉ ወታደሮቹ ልዩ መብቶች ለመስጠት የሚያስችለውን ውሳኔ አሳለፈ።
የውሳኔ ሃሳቡ የቀረበው በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "ዩናይትድ ሩሲያ" ፓርቲ ሲሆን ፤ በሀገሪቱ “ዱማ” ወይም ፓርላማ ተቀባይነት ማግኘቱንም ተነግሯል።
የተላለፈው የልዩ መብቶቸ ውሳኔ ወርሃዊ ከፍያ፣ የታክስ ጥቅማጥቅሞች፣ የተሻለ የጤና አገልግሎት እና ነጻ የህዝብ ትራንስፖርት አግልግሎትን የሚያካትት ነው።
የሩስያ መንግስት ውሳኔ፤ የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ በየ ግንበሮች እየተፋለሙ የሚገኙትን ወታደሮች ሞራል እና ወኔ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር የሚያደርግ ነውም ተብሎለታል፡፡
የወታደሮቹ ልዩ መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ 50 ሚልየን የአሜሪካን ዶላር እንደመደበም የሩሲያ መንግስት ይፋ አድርጓል።
ሩሲያ ጎረቤቷ ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከፈረንጆች የካቲት 24፤ 2022 ጀምሮ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯ ይታወቃል።
አራት ሳምንታት ባስቆጠረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመሰደድ እንደተገደዱ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ከጀምሩም ቢሆን የተቃወሙት ምዕራባውያን፤ ሩሲያን ያዳክማሉ ያሉዋቸው ማዕቀቦች ሲጥሉ እየተስተዋሉ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ ማጸደቁም እንዲሁ የሚታወስ ነው።