ሩሲያ ከሞስኮው የሙዚቃ ድግስ ጥቃት ጋር በተያያዘ 20 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አዋለች
ባለፈው መጋቢት ወር ለተፈጸመው ለጥቃቱ አይኤስ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ገልጾ ነበር
የሩሲያው ኤፍኤስቢ ኃላፊ ከጥቃቱ ጀርባ የዩክሬን እጅ አለበት የሚለውን ቀደም ሲል የቀረበውን ክስ ደግመውታል
ሩሲያ ከሞስኮው የሙዚቃ ድግስ ጥቃት ጋር በተያያዘ 20 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አዋለች።
ከ140 በላይ ሰዎች ከተገደሉበት የሞስኮው የሙዚቃ ድግስ ጥቃት ጋር በተያያዘ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሩሲያ ሴኩሪቲ ሰርቪሰ(ኤፍኤስቢ) ኃላፊ ተናግረዋል።
ባለፈው መጋቢት ወር ለተፈጸመው ለዚህ ጥቃት እስላሚክ ስቴት(አይኤስ-ኮራሳን) ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ገልጾ ነበር።
ነገርግን የሩሲያው ኤፍኤስቢ ኃላፊ አሌክሳንደር ቦርቲኒኮቭ ይህ ነው የሚባል መረጃ ባያቀርቡም ከጥቃቱ ጀርባ የዩክሬን እጅ አለበት የሚለውን የሩሲያ ክስ ደግመውታል።
"ምርመራው አሁንም እንደቀጠለ ነው፣ ነገርግን የዩክሬን ወታደራዊ ስለላ በቀጥታ ተሳትፏል ለማለት የሚያስደፍር ነው" ሲሉ ኃላፊው ለሩሲያ ታሴ የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
ክርከስ ሲቲ ኸል በተባለው አዳራሽ ላይ የተቃጣው ጥቃት በሩሲያ በ20 አመታት ውስጥ የተፈጸመ ከባድ ጥቃት ተብሎ ተመዝግቧል።
ወደ ዩክሬን ጣታቸውን የቀሰሩት ቦርቲኒኮቭ፣ የአይኤስ ቡድን የአፍጋኒስታን ክንፍ ኮራሳን ጥቃቱን በኢንተርኔት አማካኝነት በማዘጋጀት እና ፋይናንስ በማድረግ መሳተፉን ገልጸዋል።
የዩክሬን ወታደራዊ ደህንነት ምክትል ኃላፊ አንድሬ ዩሶብ "የሩሲያ ፕሮፖጋንዳ የክሮከስን ሁነት መርሳት አይፈልግም። ዩክሬን ተሳትፋለች የሚለውን የማይረባ ክስ ማሰማቱን ይቀጥላል"ሲሉ ክሱን አጣጥለውታል።
ሩሲያ ጥቃቱ በተፈጸመ በማግስቱ አራት የቻጂካስታን ዜግነት ያላቸውን ተጠርጣሪዎች መያዟን ይታወሳል።
ሩሲያ ጥቃት አድራሾቹ ወደ ዩክሬን ሊያቀኑ ሲሉ እንደያዘቻቸው በመግለጽ ነበር በዩክሬን ላይ ክስ ያቀረበችው።