አሜሪካ የተኩስ አቁም እርምጃው “ግጭቱን የሚያስቆም ከሆነ” መልካም እርምጃ መሆኑን ገለጸች
የትግራይን ግጭት ጉዳይ “ፖለቲካዊ መፍትሄ” አንደሚሻውም የአፍሪካ ህብረት ገልጿል
የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት “በተናጠል ተኩስ ለማቆም” መወሰኑን አስታውቋል
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ “ግጭቱን የሚያስቆም ከሆነ” በአዎንታ የሚታይ መሆኑን ገለጸች::
የኢትዮዮያ መንግስት በትግራይ ጉዳይ በተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃን መውሰዱ ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መግለጫ አውጥቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ በኔድ ፐራይስ የተኩስ አቁም ሂደቱ ግጭትን ካስቆመ፣ እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፎች ያለ ገደብ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲደርስ ለማድረግ ካስቻለ ውጤታማ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለመጠበቅ እንዲሁም በትግራይ መረጋጋት እንዲመጣ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሜሪካ ጠይቃለች፡፡
ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግን በጥብቅ እንዲያከብሩ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ተጠያቂነት እንዲኖሩባቸው መደረግ እንደሚገባ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
አሜሪካ በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በትብበር ለመስራት ዝግጁነት እንዳላትም ገልጻለች፡፡
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው እርምጃ ግጭቱን ለማቆም የሚያስችል ትክክለኛ እርምጃ ነው ብሏል፡፡
ለተወሰደው የተኩስ አቁም እርምጃ እውን መሆንና በትግራይ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የመንግስት ባለስልጣናት ሊሰሩ እንደሚገባም የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ሞሀማት ጥሪ አቅርቧል፡፡
የትግራይን ግጭት ጉዳይ ፖለቲካዊ መፍትሄ አንደሚሻና የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፍን የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም ሊቀ መንበሩ አስታውቀዋለ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከጊዝያዊ አስተዳደር ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽና ባወጣው መግለጫ “በተናጠል ተኩስ ለማቆም” ወስኗል፡፡
በመንግስት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም የትግራይ ኃይሎች መቀለ ከተማ መቆጣጠራቸው እየተነገረ ነው፡፡
በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት 350 ሺህ ዜጎችን ለረሀብ አደጋ ያጋለጠ እና ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ የፈጠረ መሆኑን ተመድ ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት ግን በትግራይ ረሀብ የሚባል ነገር የለም ሲል በተለያያ ጊዜያት ሲገልፅ ቆይቷል፡፡