ሩሲያ በቅርብ ሳምንታት በምስራቅ በኩል ተጨማሪ ቦታዎችን ለመቆጣጠር እያደረሰች ያለውን ጥቃት አጠናክራለች
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የምትገኝ ከተማ መቆጣጠሯን ገለጸች።
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ማሪንካ የተባለችውን ከተማ መሉ በመሉ መቆጣጠሯን ገልጻች።
ነገርግን ዩክሬን ሀሰት ነው ስትል አስተባብላለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር ባደረጉት ስብሰባ "ጦራችን በዛሬው እለት ማሪንካን መሉ በመሉ ነጻ አድርጓል"ብለዋል።
ፑቲን ከዶኔስክ ከተማ በደቡም ምዕራብ በከሉ በአምስት ኪሎሜትር ላይ የምትገኘውን ከተማ መቆጣጠር፣ ለሩሲያ ኃይሎች የጠላትን ጦር ከዶኔስክ ለማራቅ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ነገርግን የዩክሬን ጦር ቃል አቀባይ ኦሌክሳንደር ሽቱፑን ከተማዋን ላለማስደፈር ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው ሲሉ ለዩክሬን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ "ወታደሮቻችን በማሪንካ ከተማ አስተዳደር ድንበር ላይ ናቸው፤ ከተማዋን ለመከላከል ውጊያው ቀጥሏል"ብለዋል።
"ከተማዋ መሉ በመሉ ወድማለች፣ ነገሮግን ተይዛለች የሚለው ስህተት ነው"
ሩሲያ በቅርብ ሳምንታት በምስራቅ በኩል ተጨማሪ ቦታዎችን ለመቆጣጠር እያደረሰች ያለውን ጥቃት አጠናክራለች።
የዩክሬን ኃይሎች የሩሲያን ጥቃት ለመከላከል ጠንካራ ምሽጎች ሰርተው ነበር።
ሞስኮ ከተማዋን መያዟ እውነት ከሆነ ከባለፈው ግንቦት ወዲህ ለሩሲያ ትልቅ ስኬት ነው ተብሏል።
22 ወራትን ባስቆጠረው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት እጅግ ደም አፋሳሽ በተባለው ጦርነት ሩሲያ ባለፈው ግንቦት ወር ባክሙት ከተማን መቆጣጠር ችላለች።
ዩክሬን በሩሲያ የተያዙ ቦታዎችን ለማስለቀቅ በሰኔ ወር የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ብትከፍትም፣ ይህ ነው የሚባል ውጤት አላመጣችም።