የማስወንጨፊያ ስርአቱ በርካታ የተኳሾች ያሉት ሚሳይል የተገጠመለት እና እስከ 11ሺ ኪሎሜትር የሚርቁ ኢላማዎችን መምታት የሚችል ነው ተብሏል
የሩሲያ ኃይሎች የያርስ ተንቀሳቃሽ የኑክሌር ሚሳይል ማስወንጨፊያ ስርአት ልምምድ ማድረጓ ተገልጿል።
ሩሲያ ይህን ልምምድ ስታደርግ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ሮይተርስ የሩሲያ መገናኛ ብዙኻንን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሚሳይል ማስወንጨፊያ ስርአቱ (ላውንቸር) ሰራተኞች ከሞስኮ በምስራቅ አቅጣጫ 700 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የቮልጋ ወንዝ ተፋስስ የማስመሰል ወይም ከተጠላት እይታ የመሰወር እና የማንቀሳቀስ ልምምድ አድርገዋል ተብሏል።
ይህ ልምምድ የተካሄደው በነሀሴ ወር መጀመሪያ ላይ በሁለት የተለያዩ ግዛቶች የተካሄዱትን ተመሳሳይ ልምምዶች እና ሩሲያ በቤላሩስ ድንበር የታክቲካል ኑክሌር የጦር መሳሪያ ልምምድ ካደረገችበት ከሁለት ወር ገደማ በኋላ ነው።
ሮይተርስ የሩሲያውን ኮመርሳንት ጋዜጣ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ የማስወንጨፊያ ስርአቱ በርካታ የተኳሾች ያሉት ሚሳይል የተገጠመለት እና እስከ 11ሺ ኪሎሜትር የሚርቁ ኢላማዎችን መምታት የሚችል ነው።
ስርአቱ መኪና ላይ የሚገጠም ወይም መሬት ላይ ሊጠመድ የማችልም ነው።
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተችበት ከፈረንጆቹ የካቲት 2022 ወዲህ ብቻዋን፣ ከቻይ እና ሰሜን ኮሪያ ጋር በመሆን በርካታ ወታደራዊ ልምምጆችን አድርጋለች። ሞስኮ፣ ሩሲያ እና ዩክሬንን ከምታዋስነው የቅርብ አጋሯ ቤላሩስ ጋርም የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድም ጨምራለች።
በዩክሬን እያደረገችው ባለው ጦርነት ምክንያት ከምዕራባውያን ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገባቸው ሩሲያ፣ በቤላሩስ የታክቲካል ኑክሌር ሚሳይል መላኳ ይታወሳል።
ይህ የሩሲያ እርምጃ ያሰጋት አሜሪካ ወደ አውሮፓ የረጅም ርቀት ሚሳይል እንደምትልክ በቅርቡ ገልጻለች።