ሩሲያ በዶኔስክ ግዛት ሎዙቫትስኬ የተባለችውን መንደር ተቆጣጠርኩ አለች
የዩክሬን ጦር መንደሯ በሩሲያ ተይዛለች ስለተባለው ረፖርት ያለው ነገር ባይኖርም፣ በቦታው ከባድ ውጊያ ሲካሄድ አንደነበር ገልጿል
የሩሲያ ኃይሎች ቁልፍ የተባለችውን የአብዲቪካ ከተማ ከተቆጣጠሩ በኋላ በምስራቅ ዩክሬን በሚገኘው የዶኔስክ ግዛት ቀስበቀስ ወደፊት እየገፉ ናቸው
ሩሲያ በዶኔስክ ግዛት ሎዙቫትስኬ የተባለችውን መንደር ተቆጣጠርኩ አለች።
የሩሲያ ኃይሎች በዶኔስክ ግዛት ውስጥ 29 ወራት ባስቆጠረው ጦርነት ከባድ ውጊያ የተካሄደባትን ሎዙቫትስኬ የተባለችውን መንደር መቆጣጠራቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዩክሬን ጦር መንደሯ በሩሲያ ተይዛለች ስለተባለው ረፖርት ያለው ነገር ባይኖርም፣ በቦታው ከባድ ውጊያ ሲካሄድ አንደነበር ገልጿል።
የሩሲያ ኃይሎች ባለፈው የካቲት ወር ቁልፍ የተባለችውን የአብዲቪካ ከተማ ከተቆጣጠሩ በኋላ በምስራቅ ዩክሬን በሚገኘው የዶኔስክ ግዛት ቀስበቀስ ወደፊት እየገፉ ናቸው። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው የሩሲያ ኃይሎች በሩሲያ ቁጥጥር ስር ካለው የግዛቱ ማዕከል በሰሜን ምዕራብ የምትገኘውን ሉዙቫትስኬን ተቅጣጥረዋል።
በተጨማሪም ጦሩ በሎዙቫትስኬ አቅራቢያ ባሉ ሌሎች ቦታዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እና ከዩክሬን በኩል የተሞከሩ ሶስት የመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የዩክሬን ባለስልጣናት 1000 ኪሎሜትር በሚሸፍነው የውጊያ ግንባር የሎዙቫትስኬ የምትገኝበት ቀጣና ከባድ ውጊያ እየተካሄደበት እንደሚገኝ ለሳምንታት ሲገልጹ ቆይተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በዚህ ግንባር ስላለው ውጊያ ከሀገሪቱ ዋና ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲርስኪ ጋር ባለፈው ሀሙስ እለት ሁለት ጊዜ ተወያይተው ነበር ተብሏል። ባለፈው ቅዳሜ ደግሞ የዩክሬን ጦር 17 ጥቃቶችን መመከቱን እና 10 የሚሆኑ ግጭቶች ደግሞ እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
ሩሲያን ከግዛቷ ማስወጣት እንደምትችል የምትገልጸው ዩክሬን የምዕራባውያን ወታደራዊ እርዳታ እንዳይቋረጥባት ትፈልጋለች።
ምዕራባውን ሀገራት፣ ዩክሬን በልገሳ ባገኘቻቸው የረጅም ርቀት ሚሳይሎች ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ ፈቅደውላታል።
ሩሲያ ይህን የምዕራባውያን ውሳኔ "በእሳት መጫወት" ስትል መግለጿ ይታወሳል። ምዕራባዊያን ሀገራት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከማድረግ አልፈው፣ በጦርነቱ ቀጥታ የሚሳተፉ ከሆነ ሶስተኛው የአለም ጦርነት ይቀሰቀሳል ስትልም ሩሲያ በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች።