በኦሎምፒክ የመጀመርያ ቀን ምን አዳዲስ ነገሮች ተከሰቱ?
ከ10,500 በላይ አትሌቶች ለ329 የወርቅ ሜዳልያዎች የሚያደርጉት አለምአቀፋዊ ውድድር ዛሬ መካሄድ ጀምሯል፡፡
329 የውድድር ክንውኖች በመካሄዱበት ኦሎምፒክ ቻይና ቀዳሚውን የወርቅ ሜዳልያ መውሰድ ችላለች፡፡
በመጀመርያው ቀን በተካሄደው የወንዶች የኢላማ ተኩስ ውድድር እና “በስፕሪንግ ቦርድ ዳይቪንግ” የዋና አይነት ውድድር በሴቶች ወርቅ አግኝታለች፡፡
በተመሳሳይ አሜሪካ በስፕሪንግ ቦርድ ዳይቪንግ በሴቶች የብር ሜዳሊያ ስትወስድ እንግሊዝ የነሀስ ሜዳልያ በመውሰድ የመጀመርያዋ ሀገር ሆናለች፡፡
በሴቶች የ400 ሜትር ነጻ ቀዘፋ የዋና ውድድር የአውስትራሊያዊቷን አሪያና ቲትመስ በክብረወሰን የተመዘገበ ሰአት በማሻሻል አሜሪካዊቷ ኬቲ ሊዴኪይ ወደ ፍጻሜው ማለፏን ስታረጋግጥ ለወርቅ ሜዳልያውም ከፍ ያለ ግምት አግኝታለች፡፡
በቅርጫት ኳስ ውድድር አውስትራሊያ የስፔን ብሄራዊ ቡድንን በማሸነፍ በደረጃው በሁለተኛነት ተቀምጣለች፡፡
በቶክዮ ኦሎምፒክ የነሀስ ሜዳሊያ በመያዝ ያጠናቀቀው የአውስትራሊያ የቅርጫት ኳስ ቡድን በዘንድሮው ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ከሚገመቱ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡
በዛሬው እለት 13 የወርቅ ሜዳልያ የሚያስገኙ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ቻይና ሁለት ወርቆችን መውሰዷን ተከትሎ፤ ጅዶ ፣ የ 400 ሜትር ነጻ ቀዘፋ የዋና የፍጻሜ ውድድር ፣ ራግቢ እና የቤት ውስጥ ብስክሌት ውድድርን ጨምሮ 11 የወርቅ ሜዳሊያ ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡
በፓሪስ እየጣለ የሚገኝው ከፍተኛ ዝናብ በዛሬው እለት ይደረጉ የነበሩት የሜዳ ቴንስ እና የስኬት ቦርድ ውድድሮች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆኗል፡፡
በዘንድሮው ውድድር መነጋገርያ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ፈረንሳይ በትላንትናው እለት ያዘጋጀችው የመከፍቻ ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡
የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን እና ተዋቂ ግለሰቦች የመክፈቻ ፕሮግራሙን በማሞካሸት እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
የ2028ቱ ኦሎምፒክ አዘጋጅ ሀገር የሆነችው አሜሪካ ቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደን ከዚህ የሚበልጥ የመክፈቻ ፕሮግራም ማዘጋጀት ሊከብድ ይችላል ሲሉ ፈረንሳይን አድንቀዋል፡፡
ከተለመደው የስታድየም ውስጥ መክፈቻ ለየት ባለ ሁኔታ በመክፈቻው የ206 የኦሎምፒክ ልኡካን ቡድንን በመወከል ከ6ሺህ እስከ 7ሺህ አትሌቶች በ94 ጀልባዎች በሴን ወንዝ ላይ 6 ኪሎ ሜትር በማቋረጥ ወደ አይፍል ታወር አቅንተዋል።
በመክፈቻው ተዋቂዎቾ አቀንቃኞች ሲሊንዲዮን እና ሌዲ ጋጋ አድናቆትን የተቸረው ሙዚቃ አቅርበዋል።
ከአራት አመታት ወዲህ ወደ መድረክ የተመለሰችው ሲሊንድዮን በመክፈቻው ላይ ለነበራት አቀራረብ የወርቅ ሜዳሊያ ይገባታል ሲል ኒዮርክ ታይምስ ጽፋል።