ሩሲያ ከፊል ተኩስ አቁም አወጀች
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር፡ አዋጁ የሰብአዊ እርዳታን ለማንቀሳቀስ የሚያስችሉ ኮሪደሮችን ክፍት ለማድረግ ያለመ ነው ብሏል
ተኩስ አቁሙ ማሪፖል እና ቮልኖቫካ በተባሉ ሁለት የዩክሬን ከተሞች ላይ የታወጀ ነው
ሩሲያ ማሪፖል እና ቮልኖቫካ በተባሉ ሁለት የዩክሬን ከተሞች ላይ ከፊል የተኩስ አቁም አወጀች፡፡
ሩሲያ በሁለቱም የዩክሬን ከተሞች ላይ ከፊል የተኩስ አቁም ያወጀችው የሰብአዊ እርዳታ ለማንቀስቀስ የሚያስችሉ ኮሪደሮችን ክፍት ለማድረግ በሚል እንደሆነም ነው የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
ሚኒሰቴር መስርያ ቤቱ "በሞስኮ አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሰአት ጀምሮ ሲቪሎች የማሪፖል እና ቮልኖቫካ ከተሞች ለቀው እንዲወጡና የተኩስ አቁም እና የሰብአዊነት ኮሪደሮች እንዲከፈቱ በሩሲያ በኩል ከፊል ተኩስ አቁም ታውጇል" ሲልም ነው የገለጸው፡፡
የማሪፖል ከንቲባ ቫዲም ቦይቼንኮ ከተማይቱ የሩሲያ ኃይሎች ላለፉት ቀናት በተደጋጋሚ ሲሰነዝርባት በቆየ ከባድ እና ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት “ከበባ” ውስጥ መሆኗን ከሰአታት በፊት ገልጸው ነበር፡፡
ቫዲም ቦይቼንኮ "ማሪፑልን ከከበባ በማውጣት ሰብአዊ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙበት ሁሉንም መንገዶች እንፈልጋለን" ሲሉም ነበር የሰብዓዊ ቀውሱ አሳሳቢነት የገለጹት ።
የማሪዮፖልን ከተማ ለቀናት በከበባ ውስጥ በቆየችበት ወቅት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ በሌኒንግራድ ከተማ ያደረገውን በሚያስታውስ መልኩ፤ የሩሲያ ጦር ኃይሎች የከተማዋ የኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ውሃ፣ ማሞቂያ እና ማጓጓዣ አገልገሎት እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቪላድሚር ፑቲን ጦር በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማድረግ ከጀመረበት የካቲት 24 ወዲህ በርካታ የዩክሬይን ከተሞችን መደብደባቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን መገደላቸው እንዲሁም በአውሮፓ ትልቁን የአቶሚክ ኃይል ማመንጫ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ የሚታወቅ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተወደደላት አይመስልም፡፡
በዚህም አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምዕራቡ ዓለም ሀገራትና አጋሮቻቸው የሩሲያ አካሄድን ለመግታት ሀገሪቱ ያዳክማሉ ያሏቸው በርካታ ምጣኔ ሃብታዊ ማዕቀቦች በሩሲያ ላይ እየጣሉ ይገኛሉ፡፡