ክልከላው በዓለም የድመቶች ፌዴሬሽን ነው የተጣለው
ዓለም አቀፍ የድመቶች ፌዴሬሽን የሩሲያ ድመቶች በዓለም አቀፍ የትርዒት መድረኮች ላይ እንዳይሳተፉ አገደ፡፡
ፌዴሬሽኑ ሩሲያ ዩክሬንን ወራለች በሚል ነው በትርዒቶቹ እንዳትሳተፍ ያገደው፡፡
በሩሲያ ውስጥ የተዳቀሉ ድመቶችን ያካትታል የተባለለት እገዳው እስከተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ወርሃ ግንቦት መጨረሻ እንደሚቆይም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በሩሲያ የሚገኙ የትኛውም ትርዒት አቅራቢዎች በየትኛውም ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው የትርዒት መድረኮች አይሳተፉምም ብሏል፡፡
ከተመሰረተ 70 ያል ዓመታትን ያስቆጠረው ፌዴሬሽኑ በ40 ሃገራት የሚንቀሳቀሱ የድመት ትዕንት አዘጋጆችን በአባልነት አቅፏል፡፡
የዩክሬኑ ጦርነት ቀጥሏል፡፡ በጦርነቱ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት ሃገራት ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ ሲሰደዱም ድመትን ጨምሮ ሌሎች የቤት እንስሳቶቻቸውን ይዘው ነው፡፡ ይህም ነው በሩሲያ ላይ እርምጃዎችን እንዲወስድ ያስገደደው እንደ ፌዴሬሽኑ ገለጻ፡፡
በዩክሬን ለሚገኙ ድመት አርቢና አዳቃዮች ድጋፍ አደርጋለሁም ብሏል ዩክሬናውያን ተፈናቃዮችን የደገፉ ሃገራትንና ተቋማትን ያመሰገነው ፌዴሬሽኑ፡፡
ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ ከ200 ሺ በላይ ድመቶችን የሚያሳትፉ 700 ያህል ትርዒቶችን እንደሚያዘጋጅ ከድረገጹ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
አውሮፓ እና ሌሎች ምዕራባዊ ሃገራት በአሜሪካ ፊት አውራሪነት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችንና ሌሎች እገዳዎችን እያዘነቡ መሆኑ ይታወቃል፡፡