ኪየቭ የሩሲያን ወታደራዊ መሰረተ-ልማት ማውደም ለመልሶ ማጥቃቱ ወሳኝ መሆኑን ተናግራለች
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር በክሬሚያ ላይ የተቃጣውን የዩክሬን የድሮን ጥቃት ማክሸፉን አስታውቋል።
በጥቃት ሙከራው ዩክሬን 20 ድሮኖችን መጠቀሟን የገለፀው የመከላከያ ሚኒስቴሩ ሁሉም ድሮኖ መውደማቸውን እንዲሁም የተጎዳ ሰው ወይም የወደመ ነገር እንደሌለ ሚንስቴሩ ገልጿል።
ከዩክሬን በሞስኮ በተጠቀለለችው ክሬሚያ ላይ የተቃጣው ጥቃት ኢላማ ምን እንደሆነ ግልጽ አልተደረገም።
የክሬሚያ ባለስልጣናት የሞስኮ የአየር መከላከያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃትን በመከላከል ላይ ተሰማርተው እንደነበር ቀደም ብለው ተናግረዋል።
የክሬሚያ የትራንስፖርት ባለስልጣን ጥቁር ባህርን ከሩሲያ ክራስኖዳር ክልል ጋር የሚያገናኘው የክሬሚያ ድልድይ ለሁለት ሰዓታት ዝግ መደረጉን ገልጸዋል።
ካለፈው መጋቢት ጀምሮ ዩክሬን በሞስኮ በተያዙ ግዛቶቿና በክሬምሊን ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት አድርሳለች።
ሆኖም ዩክሬን ለጥቃቶቹ በግልጽ ኃላፊነት ስትወስድ አትታይም ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ኪየቭ የሩሲያን የውትድርና መሰረተ-ልማት ማውደም ለመልሶ ማጥቃቱ ወሳኝ መሆኑን ግን ተናግራለች።
ሞስኮ ክሬሚያን በ2014 ከዩክሬን ነጥቃ ወደ ራሷ ግዛት ጠቅልላለች።