ሩሲያ ምእራባውያን ለዩክሬን የለገሱትን መሳሪያ የያዘ መጋዘን አወደመች
የሩሲያ ጦር ካሊበር በተባለ ከሩዝ ሚሳዔል ነው ዩክሬንን የጦር መጋዘን ያወደመው
ሩሲያ ሶስት የዩክሬን SU-25 ተዋጊ ጄቶችን መትታ መጣሏን አስታወቀች
ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ የሚገኝ ግዙፍ ወታደራዊ መጋዘን ማውሟን የሀገሪቱ ጦር አስታውቋል።
የሩሲያ ጦር ያወደመው መጋዝን ምእራባውያን ለዩክሬን የሰጡትን በርካታ የጦር መሳሪያው የያዘ መሆኑንም የሩሲያው ኢንትራፋክስ የዜና ኤጀንሲ አስነብቧል።
የሩሲያ ጦር በቴርኖፒል ክልል ውስጥ የሚገኘውን መጋዝን ለማውደም ካሊበር በተባለ ከሩዝ ሚሳዔል መጠቀሙንም የኢንትራፋክስ ዘገባ ያመለክታል።
በተጨማሪም የሩስያ ሃይሎችም ሶስት የዩክሬን SU-25 ተዋጊ ጄቶችን በምስራቅ ዩክሬን ዶኔትስክ እና ካርኪቭ አቅራቢያ መትተው መጣላቸውን የሩሲያ መከለከያ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሩሲያ በትናትናው እለትም ሁለት ሚግ-29 የተሰኙ የውጊያ አውሮፕላኖች እና አንድ ሱ-25 የተሰኙ የውጊያ አውሮፕላኖች በካርኪቭ እና ሚኮላይቭ ግዛቶች መትታ መጣሏ ይታወሳል።
ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመለገስ ላይ ሲሆኑ፤ ሩሲያም የተለገሱትን የጦር መሳሪያዎች በማውደም ላይ መሆኗን ገልጻለች።
ከሰሞኑ ከአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የተለገሱ የጦር ተሽከርካሪዎችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ማውደሟን የሀገሪቱ ዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንዳይለግሱ አሳስበው ልገሳቸውን ከቀጠሉ ግን እርምጃ መውሰዴን እንደሚቀጥሉማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች 107 ቀናት ተቆጥረዋል።