የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 107ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
ሩሲያ ሶስት የዩክሬን የጦር አውሮፕላኖችን መታ መጣሏን ገለጸች፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች 107 ቀናት ተቆጥረዋል።
ሩሲያም በዛሬው ዕለት ከደቂቃዎች በፊት ሶስት የዩክሬን ተዋጊ አውሮፕላኖችን መትታ እንደጣለች ሮይተርስ በሰበር ዜና ዘግቧል፡፡
እንደ ሩሲያ መከላከያ መግለጫ ከሆነ ሁለት ሚግ-29 የተሰኙ የውጊያ አውሮፕላኖች እና አንድ ሱ-25 የተሰኙ የውጊያ አውሮፕላኖች በካርኪቭ እና ሚኮላይቭ ግዛቶች ተመተዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የዩክሬን መንግስት እስካሁን ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን የዩክሬን ወታደሮች ከሩሲያ ጦር ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት በየዕለቱ 200 ወታደሮች እየተገደሉ መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ልዩ ረዳት ሚካሎ ፖዶሊያክ በትናንትናው ዕለት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የሩሲያ ጦር የዶምባስ እና ሉሃንስክ ግዛቶችን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ውጊያ የዩክሬን ወታደሮች በምዕራባዊያን እርዳታ ውጊያቸውን ቀጥለዋል ተብሏል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ጦርነት በተቀረው ዓለም ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ ሲሆን በተለይም የምግብ እና ነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ እያደረገ ይገኛል፡፡
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ 20 በመቶ የዩክሬን ክፍልም በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር መውደቁን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት መሰረት መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ከተሰደዱ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን መካከል 2 ነጥብ 5 ያህሉ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡በጦርነቱ እስካሁን ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ5 ሺህ በላይ ንጹሃን ደግሞ እንደቆሰሉ የዚሁ ተቋም ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በዚህ ጦርነት ምክንያት የምግብ ዋጋ ካሻቀበባቸው ሀገራት መካከል አፍሪካ አንዷ ስትሆን ከሰሞኑ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ወደ ሞስኮ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር መምከራቸው ይታወሳል፡፤
ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ ላይ ያጠመደቻቸውን ፈንጂዎች ካላነሳች ከሩሲያ እና ዩክሬን በሚገባ የስንዴ ምርት ላይ ጥገኛ የሆነችው አፍሪካ ወደ ከፋ ረሃብ ልታመራ ትችላለች ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ክጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል፡፡