ሩሲያ ከኢንስታግራም ጋር ተመሳሳይነት ያለው “ሮስግራም” የተባለ መተግበሪያ ሰራች
አዲሱ መተግሪያ ከ10 ቀናት በኋላ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል
ሩሲያ የፌስቡክ ኩባንያው ኢንስታግራም በሀገሯ እንዳይሰራ አግዳለች
የሩሱያ የቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ ፈጣለሪዎች ከኢንስታግራም ጋር ተመሳሳይነት ያለው አዲስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያ መስራታቸው ተስምቷል።
የቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ ፈጣለሪዎቹ አዲሱን የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያ የሰሩት ሩሲያ ኢንስታግራም የተባለው መተግበሪያ በሀገሯ ውስጥ እንዳይሰራ ክልከላ መጣሏን ተከትሎ የሚፈጠረውን ከፍተት ለመሙላት ተስቦ ነው ተብሏል።
አዲሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያ “ሮስግራም” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን፤ ከ10 ቀናት በኋላ ለተጠቃሚዎች እንደሚለቀቅም ታውቋል።
አዲሱ የሩሲያው ሮስግራም የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያ ከኢንስታግራም ጋር ተመሳሳይ ነው የተባለ ሲሆን፤ ሆኖም ግን ተጨማሪ አገልግሎቶችን ያካተተ እንደሆነም ተነገሯል።
ከእነዚህም ውስጥ የገቢ ማሰባሰቢያ ማከናወን የሚስችል እንዲሁም በክፍያ ብቻ የሚታዩ ይዘቶችን መጫን የሚያስችል አገልግሎቶች እንደተካተቱበትም ታውቋል።
የሩሲያ የኮሙኒኬሽን ተቆጣጣሪ ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ ኢንስታግራም በሀገሪቱ ውስጥ እንዳይሰራ መታገዱን ማስታወቁ ይታወሳል።
ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን የሚያስተዳደርው ሜታ ኩባንያ በዩክሬን ብቻ ተግባራዊ የሚሆን የጥላቻ ንግግር ፖሊሲውን በጊዜያዊነት መቀየሩን ተከትሎ ነው ሩሲያ እርምጃውን የወሰደችው።
ሜታ ኩባንያ በጥላቻ ንግግር ፖሊሲው ላይ ባደረገው ለውጥም በዩክሬን ውስጥ የሚገኙ የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች “ሞት ለሩሲያ ወራሪዎች” የሚሉ እና መሰል መልእክቶችን እንዲያሰራጩ መፍቀዱ ይታወሳል።