የሩሲያ ኃይሎች በምስራቅ ዩክሬን ሌቫድኔ የተባለች መንደር መቆጣጠራቸውን ሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ
ሌቫድኔ የሩሲያ ኃይሎች ከፍተኛ ክምችት ባለበት በዛፖሬዥያ ግዛት ከዶኔስክ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ የምትገኝ ትንሽ መንደር ነች
ጦርነቱ በተጀመረበት አካባቢ ሩሲያ ይዛት የነበረ ቢሆንም በ2023 ደግሞ ዩክሬን መልሳ መቆጣጠሯን ማስታወቋ ይታወሳል
የሩሲያ ኃይሎች በምስራቅ ዩክሬን ሌቫድኔ የተባለች መንደር መቆጣጠራቸውን ሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የሩሲያ ኃይሎች ተቆጣጥሮ መቆየት አስቸጋሪ በሆነበት በምስራቅ ዩክሬን የምትገኘውን ላቫድኔ የተባለች መንደር ተቆጣጥረዋል።
ሌቫድኔ የሩሲያ ኃይሎች ከፍተኛ ክምችት ባለበት በዛፖሬዥያ ግዛት ከዶኔስክ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ የምትገኝ ትንሽ መንደር ነች።
ጦርነቱ በተጀመረበት አካባቢ ሩሲያ ይዛት የነበረ ቢሆንም በ2023 ደግሞ ዩክሬን መልሳ መቆጣጠሯን ማስታወቋ ይታወሳል።
በምስራቅ ዩክሬን ወደፊት እየገፋች ያለችው ሩሲያ ባለፉት ሳምንታት ለሁለት አመታት ለዩክሬን ኃይሎች እንደምሽግ ስታገለግል የነበረችውን ስትራቴጂካዊቷን ቩሌዳርን ጨምሮ በርካታ መንደሮችን ተቆጣጥራለች።
ዩክሬን ባለፈው ነሐሴ ወር በምስራቅ ዩክሬን ያለውን የሩሲያ ጦር አሰላለፍ ለማዛባት በምዕራብ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት ከፍታ ነበር።
ነገርግን የሩሲያ ኃይሎች በተቃራኒው ወደፊት በመግፋት ለዩክሬን ጦር የሎጂስቲክ ማከፋፈያ ወደ ሆነችው ወሳኟ ከተማ ፖክሮቭስክ መቅረብ ችለዋል።
ዩክሬን ምዕራባውያን ሀገራት የለገሷትን የረጅም ርቀት ሚሳይሎች ከግንባር ርቆ ሩሲያ ግዛት ውስጥ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን እና የነዳጅ መሰረተልማቶችን ለመምታት እንድትጠቀምበት እንዲፈቅዱላት በመጠየቅ ላይ ነች
ለዩክሬን ቀዳሚ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ አቅራቢ የሆነችው አሜሪካ ጉዳዩን እንደምታጤነው ብትገልጽም፣ እስካሁን ይሁንታዋን አልቸረችም።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባዊያን ዩክሬን የሩሲያን ምድር እንድትመታ ከፈቀዱ ከሩሲያ ጋር ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ እንደሚገቡ አስጠንቅቀዋል።