የዶምባስ ግዛትን ነጻ ለማድረግ የምትንቀሳቀሰው ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የከፈተችውን ጦርነት አጠናክራ ቀጥላለች
ሩሲያ በትናንትናው እለት እንዳስታወቀችው የሩሲያ ጦር ወታደራዊ ዘመቻ በሚያካሂድባቸው በሁሉም ቦታዎች ጥቃቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቃለች፡፡
በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ዩክሬንን ከተሞች በሚሳየልና በሮኬት እየደበደበች ሲሆን በጥቃቱ ከ10 በላይ ሰዎች መገደላቸው ዩክሬን እየገለጸች መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በዩክሬን የካርኪቭ ግዛት አስተዳዳሪ ኦሌህ ሲነሁቦቭ እንደተናሩት በቹሁብ ከተማ በደረሰ የሚሳየል ጥቃት የ70 አመት አዛውንትን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል፡፡
በደቡብ እና በማእከላዊ ዩክሬን የሚገኙት ከተሞቿ የሩሲያ ሚሳየል ሰለባ ሆነዋል ያለችው ዩክሬን ጥቃቱ አሁንም ይቀጥላል ስትል ስጋቷን ገልጻለች፡፡ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጊ ሶይጉ ዩክሬን በሩሲያ በተያዙ የምስራቅ ዩክሬን ቦታዎች ላይ የምታደርገውን ጥቃት ለመከላከል ጥቃቱ እንዲጠናከር መታዘዙን ገልጸዋል፡፡
ዩክሬን በምስራቅ ዩክሬን የሩሲያ የጦር ይዞቻዎችን እየመታች መሆኑን ብትገልጽም ሩሲያ ግን የሲቪል መሰረተልማቶችን ነው ስትል አስተባብላለች፡፡ የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ በሩሲያ የጦር የማጥቃት አቅም ላይ ጉዳት አስከትሏል ብሏል፡፡
ሩሲያ የኔቶ ጦር ወደ ቀድሞ የሶቬት ሀገራት መስፋፋት ለደህንነቷ እንደማያሰጋት በመግለጽ ነበር በዩክሬን ላይ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ያወጀችው።
ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬንን ትጥቅ ማስፈታት እና የናዚን አስተሳሰብ ማጥፋት የዘመቻው አላማ መሆኑን ሩሲያ መግለጿ ይታወሳል።
በሩሲያ ርምጃ የተቆጡት ምእራባውያን ሩሲያን ያዳክማል ያሉትን ሁሉ ማእቀብ በሩሲያ ላይ ጥለዋል።
የዶንቴክስ እና ሉሃንስክ ግዛቶችን የሚያጠቃልለውን የዶምባስ ግዛት ነጻ ለማውጣት መወሰኗን የምትገልጸው ሩሲያ፣በደቡብ እና ምሰራቃዊ ዩክሬን ከባድ ጦርነት እያካሄደች ትገኛለች፡፡