ሩሲያ በፈጸመችው መጠነሰፊ ጥቃት የዩክሬንን የኃይል መሰረተልማት ማውደሟን ኪቭ ገለጸች
ዩክሬን የሩሲያን ጦር ለማዛባት የሩሲያን ድንበር በመጣስ ድንገኛ ጥቃት ብትከፍትም፣ የሩሲያ ኃይሎችን በምስራቅ በኩል ወደ ፊት ከመግፋት አላስቆማቸውም
ሩሲያ ከ100 በላይ የሚሳይል እና 100 ገደማ የድሮን ጥቃት በማድረስ ቢያንስ አምስት ሰዎች መግደሏን የኪቭ ባለስልጣናት ተናግረዋል
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው መጠነሰፊ ጥቃት የኃይል መሰረተልማቶችን ማውደሟን ኪቭ ገለጸች።
ሩሲያ በዛሬው እለት ጠዋት ከ100 በላይ የሚሳይል እና 100 ገደማ የድሮን ጥቃት በማድረስ ቢያንስ አምስት ሰዎች መግደሏን እና የኃይል መሰረተልማቶችን ማውደሟን የኪቭ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በተወሰኑ የኪቭ ከተማ ክፍሎች ጨምሮ በብዙ ቦታዎች የኃይል እና የውሃ አቅርቦት ተቋርጧል። የዩክሬን ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ 2 1/2 አመት ባስቆጠረው ጦርነት ወስጥ ሩሲያ በአስሩ ግዛቶች ያሉ የኃይል መሰረተልማቶች ላይ ኢላማ አድርጋ ጥቃት እየሰነዘረች መሆኗን እየገለጹ ናቸው።
ሩሲያ በዩክሬን የኃይል ቋት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የጨመረችው ባለፈው ሚያዝያ ወር ሲሆን የዩክሬን ባለስልጣናት ሩሲያ ይህን የምታደርገው ህዝቡ በከፍተኛ መጠን የኃይል አቅርቦት የሚፈልግበት የክረምት ወቅት እየመጣ በመሆኑ ሆነ ብላ ነው ይላሉ።
የዛሬው የሩሲያ ሚሳይል ጥቃት በቅርብ ሳምንት ውስጥ ከተፈጸሙት ጥቃቶች ጋር ሲነጻጸር ከባድ የሚባለው ነው ተብሏል። ጥቃቱ የተፈጸመው ድንበር በማቋረጥ ወደ ምዕራባዊ ሩሲያ ግዛት ኩርስክ የገባችው ዩክሬን ድል እየቀናት መሆኑን በገለጸችበት እና የሩሲያ ኃይሎች ደግሞ በምስራቅ ዩክሬን ወደ ፊት እየገፉ ወሳኝ ወደ ሆነችው የሎጂስቲክስ ማከማቻ ከተማ ፖክሮቭስክ እየቀረቡ ባለበት ወቅት ነው።
"ይህ በቅንጅት ከተፈጸሙ ትላል ጥቃቶች ውስጥ አንዱ ነው። 100 የሚደርሱ የተለያዩ አይነት ሚሳይሎች እና 100 ገደማ ሸሀድ ድሮኖች ተተኩሰዋል።ይህ ጥቃት እንደበፊቶቹ የሩሲያ ጥቃቶች ሁሉ የንጹሀን መሰረተልማቶችን ኢላማ አድርጓል" ብለዋል ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽምይሃል እንደገጹት ከሆነ በጥቃቱ 15 ግዛቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዘለንስኪ የኃይል መሰረተልማቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።
ዩክሬን ጦርነቱ ሲጀመር የረጅም ርቀት ሚሳይል ያልታጠቀች ቢሆንም ከእዚያ ወዲህ ግን ሩሲያ ውስጥ ዘልቆ በመግባት የነዳጅ ማጣሪያዎችን እና የአየር ጦር ሰፈሮችን መምታት የሚችሉ ብዙ አይነት የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን መስራት ችላለች።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ኪቪ ከዚህ በፊት ከታጠቀቻቸው ሚሳይሎች የተሻለ ፍጥነት ያለው የረጅም ርቀት 'ድሮን ሚሳይል' ማበልጸጓን ይፋ አድርገዋል።
ኢንተርፋክስ የተባለው የዜና አገልግሎት የሩሲያን መከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ እንደዘገበዉ ከሆነ የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን የኃይል መሰረተልማቶች ላይ ኢላማቸውን የጠበቁ ጥቃቶች አድርሰዋል።
ዩክሬን የሩሲያን ጦር ለማዛባት የሩሲያን ድንበር በመጣስ ድንገኛ ጥቃት ብትከፍትም፣ የሩሲያ ኃይሎችን በምስራቅ በኩል ወደ ፊት ከመግፋት አላስቆማቸውም።