ሩሲያ በኪቭ እና በሌሎች ከተሞች ላይ ከባድ የሚሳይል ጥቃት አደረሰች
የዩክሬን የአየር ኃይል ከተወነጨፉት 35 ሚሳይሎች ውስጥ 22ቱን እና ከ23 ድሮኖች ውስጥ ደግሞ 20ዎቹን ማክሸፉን ገልጿል
በጥቃቱ ንጹሃን መገደላቸውን እና የንጹሃን መሰረተልማቶች ኢላማ መደረጋቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ተናግረዋል
ሩሲያ በኪቭ እና በሌሎች ከተሞች ላይ ከባድ የሚሳይል ጥቃት አደረሰች።
ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ላይ በዛሬው እለት ጠዋት በፈጸመችው መጠነሰፊ የሚሳይል ጥቃት በርካታ ቤቶች እና መሰረተልማቶችን ማውደሟን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የዩክሬን የአየር ኃይል እንደገለጸው ከተወነጨፉት 35 ሚሳይሎች ውስጥ 22ቱን እና ከ23 ድሮኖች ውስጥ ደግሞ 20ዎቹን አክሽፏል።
የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወሎች በመላው ዩክሬን ሲደወሉ አርፍደዋል። የኔቶ አባል የሆነችው የፖላንድ እና የአጋሮቿ የጦር ጀቶች በጥቃቱ ወቅት በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ተደርገው ነበር ተብሏል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተችበት ከፈረንጆቹ የካቲት 2022 ወዲህ ከባድ የተባለውን የአየር ጥቃት ከፈጸመች ከአንድ ሳምንት በኋላ የተፈጸመው ይህ ድብደባ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ከመመላሳቸው ጋር ተገጣጥሟል።
በጥቃቱ ንጹሃን መገደላቸውን እና የንጹሃን መሰረተልማቶች ኢላማ መደረጋቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ተናግረዋል። የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሲቭያቶሽንስኪን፣ሶሎምያንስኪ እና ሆሎሺቪስኪን ጨምሮ የሚሳይሎቹ ስብርባሪዎች ወደ ወደቁባቸው በርካታ ግዛቶች በፍጥነት ተሰማርተዋል።
ሩሲያ ባለፈው ሰኞ እለት ከ200 በላይ ሚሳይሎች አና ድሮኖችን በማስወንጨፍ ሰባት ሰዎችን መግደሏ እና የኃይል መሰረተልማቶችን ማውደሟ ይታወሳል። ኪቭ ይህን ጥቃት ከባድ ጥቃት ስትል ነበር የገለጸችው።
ሩሲያ በዩክሬን የኃይል መሰረተልማቶች ላይ የምትሰነዝረውን ጥቃት የጨመረችው፣ ዩክሬናውያን በመጭው የክረምት ወቅት ችግር ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ እንደሆነ ዩክሬን ታምናለች።
30 ወራትን ባስቆጠረው በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት፣ ሩሲያ ንጹሃን አጥቅታለች የሚለውን ክስ ታስተባብላለች።
ዩክሬን በግዛቷ የተሰማራውን የሩሲያ ኃይል አሰላለፍ ለማዛባት በማሰብ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም ኩርስክ ወደተባለችው የምዕራብ ሩሲያ ዘልቃ መግባት ችላለች። ነገርግን ይህ የዩክሬን ስሌት አልሰራም።
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን እያደረገች ያለውን ጥቃት በማጠናከር በዶኔስክ ግዛት ውስጥ የምትገኘውን ስትራቴጂካዊቷን የፖክሮቭስክ ከተማ ለመቆጣጠር ተቃርባለች።