ዩክሬን የምትመካበት ኤፍ-16 አውሮፕላን መከስከሱን ተከትሎ የአየር ኃይል አዛዡ ተባረሩ
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ የሀገሪቱን የአየር ኃይል አዛዥን ማባረራቸው ተገልጿል
አደጋው ዩክሬን አሜሪካ ሰራሽ አውሮፕላኖች በዚህ ወር እጇ ከገቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ነው ተብሏል
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የሀገሪቱን የአየር ኃይል አዛዥ ማይኮላ ኦሌሽቹክን በትናንትናው እለት ማባረራቸው ተገልጿል።
የአዛዙ መባባር ይፋ የሆነው የዩክሬን ጦር አሜሪካ ሰራሽ የሆነው ኤፍ-16 የጦር አውሮፕላንን የሩሲያን ጥቃት በመከላከል ላይ ሳለ መከስከሱን እና አብራሪውም መሞቱን ካሳወቀ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
"የአየር ኃይል አዛዡን ለመቀየር ወስኛለሁ። ለሁሉም የአየር ኃይል አብራዎች ዘላለማዊ ክብር አለኝ" ብለዋል ዘለንስኪ በሰጡት መግለጫ።
ዘለንስኪ አዛዡ ለምን እንደተባረሩ ግልጽ ባያደርጉም፣ አብራሪዎቹ መጠበቅ አለባቸው፤ ለዚህም እዙን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። የዩክሬን ጦር ዋና መምሪያ ሊዩትናንት ጀነራል አናቶሊ ክሪቮኖዝካ በጊዜያዊነት የአዛዡን ቦታ እንደሚረከቡ አስታውቋል። ለሰኞው የመከስከስ አደጋ ምክንያት ምን እንደሆነ ያልገለጸው የዩክሬን ጦር አውሮፕላኑ የተከሰከሰው የሩሲያን ጄት እየተጠጋ በነበረበት ወቅት ነው ብሏል።
ኦሌሽቹክ ባለፈው ሰኞ እለት ከአሜሪካ የመጡ አጋሮች አውሮፕላኑ የተከሰከሰበትን ምክንያት ለማወቅ በሚደረገው ምርመራ እያገዟቸው እንደሆነ ገልጸው ነበር።
ሮይተርስ የአሜሪካን መከላከያ ባለስልጣን ጠቅሶ አንደዘገበው ግጭት የተከሰተው በሩሲያ ጥቃት እንደማይመስል አና በአብራሪው የቴክኒክ ችግር ሊሆን ይችላል በሚለው ግምት ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው። ዩክሬን በዚህ ዘመቻ ምን ያህል ጄቶችን አሰማርታ እንደነበር ግልጽ አላደረገችም።
አደጋው ዩክሬን ለረጅም ጊዜ ስትጠብቃቸው የነበሩት አሜሪካ ሰራሽ አውሮፕላኖች በዚህ ወር እጇ ከገቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ነው ተብሏል።
ዩክሬን እነዚህ የጦር አውሮፕላኖች 2 1/2 ያስቆጠረውን ጦርነት ይቀይሩታል የሚል ከፍተኛ ተስፋ ጥላባቸዋለች።