ዩክሬን የሩሲያን ሀይል ለመበተን በሚል በኩርስክ በኩል የጀመረችው ውጊያ ስልት መክሸፉን ገለጸች
የኩርስክ ጥቃት የተጀመረው ሩሲያ ወደ ቁልፏ ፖክሮቭስክ ከተማ እያደረገች ያለውን ግስጋሴ ለማስቆም ነበር
ዩክሬን ፖክሮቭስክ ከተማን ካጣች ከባድ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል የጦር መሪዎቿ ተናግረዋል
ዩክሬን የሩሲያን ሀይል ለመበተን በሚል በኩርስክ በኩል የጀመረችው ውጊያ ስልት መክሸፉን ገለጸች፡፡
ከአንድ ወር በፊት ዩክሬን ሳይታሰበ በደቡባዊ ሩሲያ በኩል በምትገኘው ኩርስክ ግዛት ጥቃት መክፈቷ ይታወሳል፡፡
የዩክሬን ጦር በዚህ ግዛት በኩል ባደረገው ጥቃት ሶስት ዋና ዋና ድልድዮችን ጨምሮ በርካታ መሰረተ ልማቶችን እንዳወደመ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
600 ገደማ የሩሲያ ወታደሮችን መማረክ የቻሉት የዩክሬን ተዋጊዎች እስካሁን ድረስ 100 መንደሮችን እንደተቆጣጠሩ የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል ኦሌክሳንደር ሲርስኪ ተናግረዋል፡፡
ዋና አዛዡ የዩክሬን በኩርስክ በኩል አዲ ጥቃት የከፈተችው የሩሲያ ጦር ምስራቃዊ ዩክሬን በኩል እያደረገቀው ያለውን ግስጋሴ ለመግታት በሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“የውጊያው ዋና አላማ የሩሲያ ጦር የዩክሬን ዋና የሎጅስቲክስ ማዕከል የሆነችው ፓክሮቭስክ ከተማን ለመቆጣጠር እያደረገው ያለውን ግስጋሴ ለማስቆም በሚል ነበር፣ ይሁንና ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን ያለውን ጦሯን ከውጊያ ግንባር ከማውጣት ይልቅ አዲስ ጦር ወደ ኩርስክ ማስገባትን መርጣለች” ሲሉ ተናግረዋል ዋና አዛዡ፡፡
ዩክሬን የምትመካበት ኤፍ-16 አውሮፕላን መከስከሱን ተከትሎ የአየር ኃይል አዛዡ ተባረሩ
ዋና ኣዘዡ አክለውም ፓክሮቭስክ በሩሲያ ጦር ተያዘች ማለት በበርካታ የውጊያ ግንባር ያሉ የዩክሬን ተዋጊዎች ወደ ላለመቆረጥ ሲሉ የግድ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ይገደዳሉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ ያላትን ሁሉ ወደ ውጊያ ግንባር በመርወር ቀስ በቀስ መንደሮችን እየተቆጣጠሩ ነው ያሉት ዋና አዛዡ ዩክሬን ፓክሮቭስክን ላለማስረከብ ከባድ ውጊያ እያደረጉ መሆኑን መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፓክሮቭስክ ከተማ ባሳለፍነው የካቲት ወር ላይ ከእልህ አስጨራሽ ውጊያ በኋላ በሩሲያ ጦር የተያዘችው አቭዴቭካ ከተማ በኋላ ወሳኝ ቦታ ስትሆን ዩክሬን ይህችን ከተማ ተነጠቀች ማለት ጦሯ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ከማድረጉ ባለፈ ዶንቴስክ ግዛትን ሙሉ ለሙሉ ለሩሲያ ጦር ታስረክባለች፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን የአየር ላይ ጥቃቶችን ለማምከን ምዕራባዊያን ሀገራት ኤፍ-16 የተሰኘውን የጦር አውሮፕላን እንዲለግሷት ስትጠይቅ ቆይታለች።
ይህን ተከትሎም አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን ኤፍ-16 የተሰኘውን የውጊያ አውሮፕላን ለዩክሬን በመስጠት ላይ ናቸው።
አሜሪካ የለገሰችው የመጀመሪያው ኤፍ-16 የጦር ጀት ባሳለፍነው ሀምሌ ኪቭ ደርሷል።
እስካሁን ዩክሬን ስድስት ኤፍ-16 የጦር ጀት ከወዳጆቿ የተረከበች ሲሆን ከነዚህ መካከል አንዱ ከሰሞኑ ተከስክሷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የጦር ጀቱን ሲያበር የነበረው ኮለኔል ኦሌክሲ ሜስ የተሰኘው ፓይለት በአደጋው ምክንያት ህይወቱ እንዳለፈ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪም የሀገሪቱን አየር ሀይል ዋና አዛዥ ከሃላፊነት ያነሱ ሲሆን ኤፍ-16 የተሰኘው ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላን በስህተት በራሷ ዩክሬን እንደተመታ ተገልጿል፡፡