ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት 355 ሺህ ወታደሮችን እንዳጣች ብሪታንያ ገለጸች
የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስቴር ሩሲያ በየዕለቱ 983 ወታደሮቿን እያጣች ነው ብሏል
ብሪታንያ የተባለውን ቁጥር እንዴት እንዳሰሉት ይፋ አላደረገችም
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት 355 ሺህ ወታደሮቿን ማጣቷን ብሪታንያ ገለጸች፡፡
ለቀናት ልዩ ዘመቻ ለማድረግ በሚል የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሁለት ዓመት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሰረት ሩሲያ 355 ሺህ ወታደሮቿ ሞት እና ቁስለኞች ሆነዋል ብሏል፡፡
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ከሆነ ሩሲያ በየዕለቱ 983 ወታደሮቿ ሙት እና ቁስለኛ እየሆኑባት እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
በያዝነው ዓመት የካቲት ወር ከገባ በኋላ ደግሞ የሚገደሉ እና የሚቆስሉ የሩሲያ ወታደሮች ቁጥር ጨምሯልም ተብሏል፡፡
እስካሁን ሩሲያ እና ዩክሬን ምን ያህል ወታደሮቻቸውን እንዳጡ በይፋ ሪፖርት ያላወጡ ሲሆን ብሪታንያ የአሁኑን መረጃ እንዴት እንዳሰላችው ከመናገር ተቆጥባለች ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በያዝነው የካቲት ወር ላይ የሩሲያ ጦር አድቪቭካ የተባለችውን ቦታ ከዩክሬን የተረከበ ሲሆን ተጨማሪ ቦታዎችንም በመቆጣጠር ላይ እንደሚገኝ ሲገለጽ ዩክሬን በበኩሏ ከአካባቢዎቹ ማፈግፈጓን አስታውቃለች፡፡
ሩሲያ የጀርመን አየር ሀይል አመራሮች በሚስጢር ያወሩትን ሰነድ ይፋ አደረገች
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከቀናት በፊት 31 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን ይፋ የደረጉ ሲሆን ወታደሮቻቸው ለከፈሉት መስዋዕትነት አመስግነዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም በጦርነቱ የቆሰሉ፣ የሞቱ እና የጠፉ ወታደሮችን ጠቅላላ ድምር ጦርነቱ ሲቆም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ እስካሁን ስድስት ሺህ ወታደሮች እንደተገደሉባት ይፋ ያደረገች ሲሆን ስለቆሰሉ እና ሌሎች መረጃዎችን እስካሁን ይፋ አላደረገችም፡፡