በህዝበ ውሳኔው ውጤት የተደናገጠችው ዩክሬን ምዕራባውያንን “ትርጉም ያለው ወታደራዊ ድጋፍ አድርጉልኝ” ስትል ተማጸነች
በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኙ አራቱም የዩክሬን አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸው ተገልጿል
ኪቭ ዓለም የክሬምሊንን ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በአስቸኳይ ሊያወግዘው ይገባል ብላለች
አራቱም የዩክሬን አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገባቸው ዩክሬን፤ የምዕራቡ ዓለም ትርጉም ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ያድርግልኝ ስትል ተማጸነች፡፡
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ፤ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት፣ ኔቶ እና የቡድን ሰባት ሀገራት በአስቸኳይ እና በከፍተኛ ደረጃ በሩሲያ ላይ የሚያደርጉት ጫናና የሚጥሉት ማዕቀብ እንዲገፉበት ጠይቃለች፡፡
ዩክሬን ምእራባውያን ለዩክሬን የሚሰጡት የጦር መሳሪያ እርዳታ እንዲያሳድጉም ጥሪ ማቅረቧን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
“ዩክሬን ታንኮች፣ የውጊያ አውሮፕላኖች፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ የረዥም ርቀት መድፎች፣ ጸረ-አውሮፕላን እና ሚሳዔል መከላከያ መሳሪያዎች ያስፈልጓታል” ም ነው ያለው ሚኒስቴሩ በመግለጫው።
ሚኒስቴሩ፤ "ሁሉም መንግስታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በጊዜያዊነት በተያዙት የዩክሬን ግዛቶች ውስጥ ያለውን የክሬምሊን ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በአስቸኳይ ሊያወግዙት ይገባል"ሲልም አክሏል፡፡
በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኙ አራቱም የዩክሬን አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸው የሚታወቅ ነው፡
በዩክሬን እንዲሁም በበርካታ የምዕራባውያን ሀገራት ውግዘት የደረሰበት ህዝብ ውሳኔ ከመስከረም 13 ስከ መስከረም 17 ድረስ ተካሂዷል።
ህዝበ ውሳኔው የተካሄደው በአራት የዩክሬን ግዛቶች ላይ ሲሆን፤ ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ ሪፐብሊኮች ያካተተ ነበር።
ህዝበ ወሳኔው መጠናቀቁን ተከትሎ የሞስኮ ደጋፊ ባለስልጣናት በትናትናው እለት ድምጽ መስጠት ሂደት መጠናቀቁን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ ሪፐብሊኮች ህዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው አራቱም አካባቢዎች የሚገኙ ዩክሬናውያን ሩሲያን ለመቀላቀል ድምጽ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
የህዝበ ውሳኔው ድምጽ አሰጣጥ መጠናቀቁን ተከትሎ በተካሄደው ቆጠራም 96 በመቶ ዩክሬናውያን ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
ሞስኮ በዩክሬን ግዛቶች ላይ የምታካሂደው ህዝበ ውሳኔ በዩክሬንና ምዕራባውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቃወሞ እንደገጠመው የሚታወቅ ነው።
ኪቭ ባለስልጣናት ህዝበ ውሳኔው ህጋዊነት እንደሌለውና ተቀባይነት እንደማያገኝ ሲገልጹ መቆየታቸውም ይታወቃል።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ምርጫውን “የይስሙላ ድምጽ” ሲሉ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ “አሳፋሪ” ነው ሲሉ ገልጸውታል። አሜሪካ በበኩሏ ህዝበ ውሳኔው "የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መርሆዎችን የሚጥስ ነው" ብለዋለች።
ሩሲያ በበኩሏ ሞስኮ፤ በሩሲያ ኃየሎች ስር የሚገኙትን የዶንባስ ግዛቶችን ለመከላከል ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ጦር ማሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
የቀድሞ የሩስያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ህዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው የዶንባስ ግዛቶች ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም አደጋ ለመከላከል ፤ አስፈላጊ ነው የሚባለው የትኛውም የጦር መሳሪያ በጥቅም ላይ ታውላለች ማለታቸው ይታወሳል፡፡