ፑቲን ለሩሲያ ለሚዋጉ የውጭ ዜጎች ዜግነት እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ሰጡ
የውጭ ዜጎች ፖስፖርቱን ለማግኘት ቢያንስ ለአንድ አመት የፈረሙበትን ኮንትራት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል
ሩሲያ ምን ያህል የውጭ ዜጎች በዩክሬን ውጊያ እንዳሰለፈች ይፋ አላደረገችም
ፑቲን ለሩሲያ ለሚዋጉ የውጭ ዜጎች ዜግነት እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ሰጡ።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቬላድሚር ፑቲን በትናንትናው እለት በዩክሬን ለሩሲያ የሚዋጉ የውጭ ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው ዜግነት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ ላይ መፈረማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህ ትዕዛዝ መሰረት ሞስኮ እያካሄደች ባለችው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ወቅት ኮንትራት የፈረሙ የውጭ ዜጎች፣ ሚስቶቻቸው፣ ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው የሩሲያን ፖስፖርት ለማግኘት ማመልከት ይችላሉ ተብሏል።
የውጭ ዜጎች ፖስፖርቱን ለማግኘት ቢያንስ ለአንድ አመት የፈረሙበትን ኮንትራት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
በመደበኛው የሩሲያ ጦር እና መደበኛ ባልሆነ ጦር የተሳተፉ ሁሉ የዚህ መብት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዘገባው ጠቅሷል።
ይህ የፕሬዝደንት ፑቲን እርምጃ የውጊያ ልምድ ያላቸው የውጭ ዜጎች እንዲቀላቀሉ ለማበረታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል። ሩሲያ ምን ያህል የውጭ ዜጎች በዩክሬን ውጊያ እንዳሰለፈች ይፋ አላደረገችም።
የአሜሪካ ደህንነት ግን ሩሲያ በጦርነቱ 315ሺ ወታደሮቿ ሙት እና ቁስለኛ ሆነውባታል የሚል መረጃ አውጥቷል። ሩሲያ ከሁለተኛ የአለም ጦርነት በኋላ ባለፈው መስከረም ወር ባካሄደችው የእጩ ወታደሮች ምልመላ 300ሺ ወንዶችን መዝግባለች።
ክሬሚሊን ተጨማሪ ምልመላ እንደማያስፈልገው አስታውቋል።
22 ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት፣ ሩሲያም ሆነች ዩክሬን የተገደሉባቸውን እና የቆሰሉባቸውን ወታደሮች ቁጥር ይፋ አላደረጉም።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪም ባለፈው ወር የዩክሬን ጦር ግማሽ ሚሊዮን ተዋጊ ለመመልመል ሀሳብ ማቅረቡን ገልጸው ነበር።
የኪቭ ፖርላማ በትናንትናው እለት ይህ ሀሳብ እየመረመረው መሆኑን ገልጿል።