ግድያው በተሽከርካሪያቸው ላይ በተጠመደ ቦምብ የተፈጸመ ነው ተብሏል
የሩሲያ ጦር በተቆጣጠረው ኬርሰን ክልል የተሸሙት ከፍተኛ መሪ መገደላቻው ተገለፀ።
ዩክሬን የሰሜን ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች ዛሬ አራት ወር የሞላው ሲሆን ከ15 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
ሩሲያ ወደ ዩክሬን ግዛቶች የላከችው ጦር በርካታ የዩክሬንን ግዛቶች የተቆጣጠረ ሲሆን ከነዚህ ቦታዎች መካከል ኬርሶን አንዷ ናት።
ሩሲያም በዚህች ክልል ድሚትሪ ሳቭሉቼንኮ የተሰኘ አንድ ከፍተኛ ሰው ክልሉን እንዲያስተዳድር ሾማ የነበረ ሲሆን፤ በተሸከርካሪው ላይ በተጠመደ ቦምብ መገደሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የዩክሬን ጦር እንደዚህ አይነት ነገር ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው ግድያ ሲሆን፤ ይህ ግለሰብ የኬርሶን ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ሃላፊ ነበር ተብሏል።
ግድያውን የኬርሰን ክልል ምክትል መሪ የሆነው ኪሪል ስትሪሞሶቭ ለሮይተርስ አረጋግጧል።
ሩሲያው ዜና ወኪል ታስ በበኩሉ ግድያው ታቅዶበት የተደረገ መሆኑን ገልጾ፤ ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው ስፍራዎች የመጀመሪያው ግድያ ነው ተብሏል።
ኬርሰን ክልል ሩሲያን በሰሜን ምዕራብ ዩክሬን በኩል የምታዋስን ቦታ ስትሆን ጦርነቱ በተጀመረ የመጀመሪያው ሳምነት ላይ የሩሲያ ጦር ተቆጣጥሯት ቆይቷል።
ዩክሬን ለሩሲያ በወገኑ እና አገልግሎት እየሰጡ ባሉ ዜጎቿ ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ባሳለፍነው ሳምንት ባንዳ ነው ባለችው በቾርኖቤቭካ መንደር በአንድ ሰው ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ሰንዝራ ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡
ከሩሲያ ጋር በበርካታ ግንባሮች እየተዋጋች ያለችው ዩክሬን ወታደሮቿ ከሴቨሮዶኔስክ እንዲያፈገፍጉ ማዘዟ ይታወሳል፡፡
ኪቭ ወታደሮቿ ከሴቨሮዶኔስክ እንዲያፈገፍጉ ያዘዘችው ከተማዋ ምስራቃዊ ዩክሬንን ለመቆጣጠር በሚያስችል ከባድ ዘመቻ ላይ በሚገኘው የሩሲያ ጦር መከበቧን ተከትሎ ነው፡፡
የአካባቢው አስተዳዳሪ የዩክሬን ወታደሮች አሳልፎ ላለመስጠት በሚል ወደ ፍርስራሽነት በተቀየረችው ከተማ እና በአካባቢው የመቆየታቸው ጉዳይ ትርጉም አልባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የሴቬሮዶኔስክ በሩሲያ ወታደሮች እጅ መውደቅ ምስራቃዊ ዩክሬንን በተለይም ሉሃንስክ ግዛትን ሙሉ በሙሉ በእጇ ለማስገባቷ መንገድ የሚጠርግ ነው።